መልከ ጼዴቅ
መልከ፡ ጼዴቅ በኦሪት ዘፍጥረት ምዕራፍ 14:18-20 የተጠቀሰ ንጉሥና ቄስ ነበረ።
በዚያው ምንባብ መሠረት፣ አብራም እነኮሎዶጎሞርን ካሸነፈ በኋላ፣ የሰዶም ንጉሥ (ባላ) ምርኮውን በምላሽ እንዲቀበለው አብራምን ባገኛኘው ጊዜ፣
- «የሳሌም ንጉሥ መልከ ጼዴቅም እንጀራንና የወይን ጠጅን አወጣ፤ እርሱም የልዑል እግዚአብሔር ካህን ነበረ።
- ባረከውም፦ አብራም ሰማይንና ምድርን ለሚገዛ ለልዑል እግዚአብሔር የተባረከ ነው፤
- ጠላቶችህን በእጅህ የጣለልህ ልዑል እግዚአብሔርም የተባረከ ነው አለውም። አብራምም ከሁሉ አሥራትን ሰጠው።»
የሳሌም ሥፍራ በኋላ እየሩሳሌም የተባለው ከተማ እንደ ሆነ በአብዛኞቹ ይቀበላል።
መልከ ጼዴቅ እንደገና በመዝሙረ ዳዊት 109 (110) ይጠቀሳል፦
- «እንደ መልከ ጼዴቅ ሥርዓት
- አንተ ለዘላለም ካህን ነህ ብሎ፥
- እግዚአብሔር ማለ አይጸጸትም።»
በአዲስ ኪዳን ደግሞ ቅዱስ ጳውሎስ ወደ ዕብራውያን ሲጽፍ በ5፡6 ይህ መዝሙር ስለ መሢሕ ትንቢት መሆኑን አውቆ ይጠቅሰዋል። በምዕራፍ 6፡20 ኢየሱስ እንደ መልከ ጼዴቅ ሹመት ለዘላለም ሊቀ ካህናት የሆነው እንደ ሆነ በግልጽ ያስተምራል። በተለይ በምዕራፍ 7 ስለ መልከ ጼዴቅ ይጽፋል። የ«መልከ ጼዴቅ» ትርጉም «የጽድቅ ንጉሥ» ሲሆን «የሳሌም ንጉሥ» ደግሞ «የሰላም ንጉስ» ማለት እንደ ነበር ይገልጻል። ከአብራም የላቀ፣ አብራምም ለእርሱ አስራት የሰጠው፣ ደግሞ በዳዊት ዘላለማዊ ቄስ የተባለው ስለ ሆነ፣ የክርስቶስ አምሳል እንደ ነበረ ያሳውቀናል።
ከአብራም በቀር አሕዛብ በሙሉ አረመኔ ሲሆኑ የዚህ ዘላለማዊ ቄስ መታወቂያ ወይም ማንነት ለዘመናት ምስጢራዊ ጥያቄ ሆኖአል። በአንዳንድ በተለይ በአይሁዶች መምህራን ዘንድ፣ ይህ መልከ ጼዴቅ በእውነት የኖህ ልጅ ሴም ነበረ፣ ሹመቱም ከማየ አይህ በፊት ስለ ኖረ ነበር። ሌሎች ሊቃውንት እንደሚሉ፣ መልከ ጼዴቅ እራሱ መሲህ ነበረ፣ በአብራም ዘመን ለጊዜው ጉብኝት ያደረገው ወልድ (መሲህ) ነበር። በተጨማሪ መልከ ጼዴቅ ኢትዮጵያዊ ነው የሚል ልማድ ወይም ሃልዮ ይኖራል።
ከዚህ በላይ ከመጽሐፍ ቅዱስ ውጭ ስለ መልከ ጼዴቅ የተለያዩ ትምህርቶችና ታሪኮች አሉ።
- ኪታብ አል-ማጋል በቅሌምንጦስ ሥነ ጽሑፍ ውስጥ ይመደባል። በዚህ ጹሑፍ ዘንድ፣ ሰብአ ሠገል ብራናውን ለክርስቶስ በሕጻንነቱ እንደ ስጦታ ሰጡት፣ እሱም ለጴጥሮስ፣ ጴጥሮስም በኋላ የሮሜ ፓፓ ለሆነው ለቅሌምንጦስ ያቀረበው ታሪክ ነው። በዚህ መሠረት፣ የመልከ ጼዴቅ አባት የአርፋክስድ ልጅ ማሊኽ እንደ ነበር እናቱም ዮጻዳቅ እንደ ተባለች የአርፋክስድ አባት ሴም በጻፈው መዝገብ እንደ ተገኘ ይጨምራል። ከዚህ በላይ፣ በኖህ ትዕዛዝ ሴምና መልከ ጼዴቅ አብረው ወደ አራራት ሔደው የአዳምን ሬሳ ከኖህ መርከብ አወጡት። ከዚያ በሗላ፣ በመላዕክት ዕርዳታ ወደ ኢየሩስሌም ዞረው በጎልጎታ ኮረብታ ውስጥ አቀበሩት። አብራም በእግዚአብሔር ትዕዛዝ ይስሐቅን እንደ መሥዋዕት ወደ መሥዊያ ቦታ ባመጣው ጊዜ፣ የነበሩበት ኮረብታ ጎልጎታ ሲሆን የመልከ ጼዴቅ መሥዊያ ቦታ ነበር። ያንጊዜ የአሕዛብ ነገሥታት ስለ መልከ ጼዴቅ ዝና ሰምተው ለበረከት ወደርሱ መጥተው ነበር። እነዚህ ነገሥታት ሁሉ ወዲያው ከተማ ለመልከ ጼዴቅ ሠሩለት፣ ስሙን «እየሩሳሌም» አለው። ነጉሦቹም እንደሚከተሉ ይዘርዝራሉ፦ የጌራራ ንጉሥ አቢሜሌክ፣ የሰናዖር ንጉሥ አምራፌል፣ የዴላሳር (ኤላሳር) ንጉሥ አርዮክ፣ የኤላም ንጉሥ ኮሎዶጎምር፣ የሕዝብ ንጉሥ ቲዳል (ቲርጋል)፣ የሰዶም ንጉሥ ቤራ (ባላ)፣ የገሞራ ንጉሥ ብርሳ፣ የአሞራውያን ንጉሥ ስምዖን፣ የሳባ ንጉሥ ሲማይር፣ የቤላ (ዞዓር) ንጉሥ ቢስላህ፣ የደማስቆ ንጉሥ ህያር፣ እና የበረሃዎች ንጉሥ ያፍታር ናቸው። ከዚህም በኋላ የቴማን ንጉሥ ማዋሎን የመልከ ጼዴቅን በረከት ለማግኘት ወደ እየሩሳሌም ተጓዘ ይላል።[1]
ተመሳሳይ ዝርዝሮች የመዛግብት ዋሻ እና የአዳምና ሕይዋን ትግል ከሠይጣን ጋራ በተባሉት መጻሕፍት ይገኛሉ። በአዳምና ሕይዋን ትግል ዘንድ የመልከ ጼዴቅ አባት የአርፋክስድ ልጅ ቃይንም ነው። መጽሐፈ ንቡ የሚባለው ጽሑፍ እንደሚለው የቃይንም 2 ልጆች ሻላሕ (ሳላ) እና ማላሕ ሲሆኑ፣ ማላሕ ዮጻዳቅን አግብቶ የመልከ ጼዴቅ ወላጆች ሆኑ።
እነዚህ ምንጮች እንደሚሉን፣ ከአራራት ወደ ጎልጎታ ተመልሰው ሴም መልከ ጼዴቅን ለምንኩስና በምስጢር ሾመው። ወላጆቹ ማላሕና ዮጻዳቅ «ልጃችን ወዴት ነው?» ጠይቀው ሴም «በመንገድ ላይ ዐረፈ» ሲላቸው ዕውነት መስሎአቸው አለቀሱለት። መልከ ጼዴቅ ከሴም ሹመት በኋላ ቆዳ ለባሽ፣ ከጎልጎታ አቅራቢያ መቸም የማይራቅ፣ እንደ ናዝራዊ ጽጉሩን መቸም ያላቋረጠ ካህን ሆነ። አብራምን መጀመርያ ባገናኘው ጊዜ ግን መልከ ጼዴቅ በእግዜር ትዕዛዝ የራሱን ጥፍሮች አቋረጠ። 12 ንጉሦቹ በጽድቁና በመልካምነቱ አድንቀው ወደ አገሮቻቸው እንዲመጣ ቢለምኑት ከዚህ መራቅ አልችልም ብሎ እምቢ አላቸው። ስለዚህ በሠፈሩ እየሩሳሌምን የሠሩለት ነው። በኋላም የይስሐቅ ሚስት ርብቃ ርጉዝ በሆነችበት ሰዓት ሁለት አገራት (ማለት ኤዶምያስና እስራኤል) በማሕፀንሽ አሉ ብሎ የነበየላት መልከ ጼዴቅ እንደ ነበር በነዚህ መጻሕፍት ይነገራል።
መጽሐፈ ሄኖክ ካልእ ወይም ስላቮኒክ ሄኖክ የታወቀው ከጥንታዊ ስላቮንኛ ቅጂዎች ሲሆን በአንዳንድ ቅጂ ስለ መልከ ጼዴቅ በፍጹም የሚለዩ ልማዶች ያቀርባል። በዚህ መሠረት ከማየ አይኅ አስቀድሞ የኖኅ ወንድም ኒር ሚስት ሶፓኒም መካን ስትሆን በእርጅናዋ በድንግልናዋ በተዓምር መልከ ጼዴቅን እየወለደች ሞተች። ልጁም ዐዋቂ ሆኖ ተወለደ። ከዚያ መልአኩ ገብርኤል ወደ ኤድን ገነት ወሰደው፤ ስለዚህ መልከ ጼዴቅ በኖኅ መርከብ ላይ ሳይሆን ከጥፋት ውኃ ማምለጥ ቻለ ይላል። ይህ ታሪክ ምናልባት በዕብራይስጥ በ 60 አም ገደማ እንደ ተቀነባበረ ይታስባል።
በሞት ባሕር ወይም ቁምራን ጥቅል ብራናዎች መካከል አንዱ «የመልከ ጼዴቅ ሰነድ» ወይም 11Q13፣ እንዲሁም በኖስቲሲሲም እምነት ጽሑፎች በናግ ሐማዲ ግብጽ መካከል አንዱ፣ መልከ ጼዴቅ በፍርድ ቀን የሚመጣ የአምላክ መሲሕ መጠሪያ (ጽድቅ ንጉሥ) ነው።
የአይሁድ ግሪክኛ ታሪክ ጸሐፊዎች ፊሎ እና ዮሴፉስ (የአይሁዶች ቅርሶች) እንዳሉ፣ መልከ ጼዴቅ የእግዚአብሔር ካህን ነበር። ዮሴፉስ ግን በሌላው ታሪክ መጽሐፉ የአይሁዶች ጦርነቶች ውስጥ መልከ ጼዴቅ ከነዓናዊ አለቃ ነበር ብሎ ጻፈ።
- ^ ኪታብ አል-ማጋል (እንግሊዝኛ)