Jump to content

ትንቢተ ዳንኤል

ከውክፔዲያ
(ከትንቢተ ዳኔል የተዛወረ)

ዳንኤል የሚለው ስም "ዳን" እና "ኤል" የሚሉት የሁለት ቃላት ጥምረት ሲሆን ትርጓሜውም እግዚአብሔር ፈራጄ ወይም ዳኛዬ ነው ማለት ነው፡፡ ዳንኤልና ሦስቱ ወዳጆቹ የአይሁዳውያን ማኅበረሰብ ክፍል የነበሩና ወደ ባቢሎን በምርኮ እንደ ተወሰዱ መጽሐፉ ያትታል (ዳን1)፡፡ ዳንኤል በባቢሎን በነበረበት ጊዜ ብልጣሶር የሚል ተጨማሪ ስም ነበረው፡፡ በባቢሎናውያን ቋንቋ ብልጣሶር ማለት "ሕይወቱን ጠብቀው" ማለት ነው፡፡ ነቢዩ ዳንኤል በይሁዳ አገር ከመሳፍንት ወይም ከንጉሣዊ ቤተሰብ የተወለደ፣ የባቢሎንና የፋርስ ሥልጣኔ እጅግ በጣም ባየለበትና ዓለም በእነዚህ ሥልጣኔዎች በተወረረችበት ጊዜ የኖረ ሰው ነው፡፡

ዳንኤል በወቅቱ ከነበሩት ታላላቅ ነገሥታት ከሚባሉት ከእንደእነ ናቡከደነፆር፣ ከቂሮስና ከሜዶናዊው ዳርዮስ ጋር የሠራ ጥበበኛ አገልጋይ ነው፡፡ በተጨማሪም ዳንኤል ታማኝና ቅን አገልጋይ፣ እምነተ ጠንካራ፣ ነቢይነት ከአስተዳዳሪነት ጋር የተካነ ወጣት ነበር(ዳን 1፡3)፡፡ ዳንኤል የከለዳውያን ቋንቋና ባህል ተምሮ በንጉሡ ቤት እንደተሾመ ከመጽሐፉ እንረዳለን(ዳን 1፡3-21)፡፡ ዳንኤል የሚለው ስም በነቢዩ ሕዝቅኤል ውስጥ ከኖኅና ከኢዮብ ጋር ሁለት ጊዜ ተደጋግሞ ስለተጠቀሰ ትንቢተ ሕዝቅኤልን ያነበቡ ዳንኤል ጻድቅ እንደነበር በቀላሉ ይገነዘባሉ (ሕዝ 14፡12-23)፡፡

የመጽሐፉ ዋና ገጸ ባሕርይ የሆነው ዳንኤል ግን በ605 በምርኮ ወደ ባቢሎን የተወሰደ በመሆኑ የኖረው ከ620 ዓ.ዓ እስከ 539 ዓ.ዓ ድረስ እንደሆነና ባቢሎን ውስጥ ሞቶ እንደተቀበረ ይገመታል፡፡ ዳንኤል ባቢሎን ውስጥ በስደት በሚኖርበት ጊዜ አብረውት የተሰደዱ ሦስት ወዳጆች እንደነበሩት ይታወቃል፡፡ በስደት በነበሩበት ጊዜ የዳንኤል ሦስቱ ወዳጆችም በተመሳሳይ መልኩ ስማቸው ተቀየረ፡፡ በዚህም መሠረት ዳንኤል ብልጣሶር፣ ሐናንያ ሲድራቅ፣ ሚሳኤል ሚሳቅ፣ ዐዛርያን አብደናጎ ተብለው ተጠሩ (ዳን 1፡7)፡፡ አብደናጎ የሚለውን ስም ላይ የመጨረሻው ክፍል "ናጎ" ባቢሎናውያን ከሚያመልኩአቸው አማልክት ውስጥ የአንዱ ስም ሲሆን "ሚሳቅ" የሚለው ደግሞ ሌላ "ሚሳቅ" የሚባል የባቢሎናውያን አማልክት ስም መሆኑን ይታወቃል፡፡ በአጠቃላይ በባቢሎናውያን ንጉሥ ባለሟሎች አለቃ አማካይነት የተቀየሩት ስሞች ከባቢሎናውያን አማልክቶች ጋር የተቆራኘ ትርጓሜ ያላቸው ናቸው፡፡

የተጻፈበት ዘመን፣ ሥፍራና ይዘት

[ለማስተካከል | ኮድ አርም]

መጽሐፉ የሚሸፍነው ረዥም ታሪክ ወይም ብዙ ዘመናት ውስጥ የተከናወኑ ድርጊቶችና በተለያዩ ጊዜያት ስለተነሡት ኃያላን ነገሥታት ስለሆነ በአንድ ጊዜና በአንድ ሰው የተጻፈ ነው ለማለት ያስቸግራል፡፡ መጽሐፉ በብዙ ሊቃውንት ዘንድ ከክርስቶስ ልደት በፊት በስድስተኛው መቶኛ ክፍለ ከመን ሊጻፍ እንደሚችል ቢያምኑም ሌሎች ግን ይህንን በመቃወም ከክርስቶስ ልደት በፊት በሁለተኛው መቶ ክፍለ ዘመን እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ በሁለተኛው መቶ ክፍለ ዘመን ተጽፏል እንደሚሉት ሊቃውንት አገላለጽ፤ ትንቢተ ዳንኤል የተጻፈው እንዲያውም አንጥዮኩስ ኤጲፋኑስ አራተኛው የተባለው መሪ የግሪክን ሥልጣኔ በአይሁዳውያን ዘንድ የማስፋፋት ዘመቻውን ባጠናከረበት ወቅት እንደሆነ ይገልጻሉ፡፡ አንጥዮኩስ ኤጲፋኑስ አራተኛው ቤተ መቅደስን በማርከስና የአይሁድን ሃይማኖት በመቃወም ከፍተኛ ዘመቻ ያደረገው ከ168 እስከ 164 ዓ.ዓ ባለው ጊዜ እንደሆነ ከጽሑፉ ይዘትና ከታሪክ መዛግብት ያረጋግጣሉ፡፡

ሆኖም በክርስትናአዲስ ኪዳን ውስጥ ኢየሱስ ክርስቶስ ትንቢተ ዳንኤልን ሲጠቅስ (ማቴ 24:15)፣ የተነበየው ማርከስ ገና ወደፊት በዚህ ዓለም ወደ መጨረሻው ቀን እንደሚደርስ ዳግመኛ አረጋገጠ፤ ስለዚህ ብዙዎች ትንቢቱ ስለ አፊፋኖስ አይሆንም በማለት ያምናሉ። ዕብራይስጡ መጻሕፍት ከነአዋልድ መጻሕፍትተረፈ ዳንኤል ጭምር በ፸ ሊቃውንት ወደ ግሪክኛ ቋንቋ መተረጎሙ የተጀመረው ከአፊፋኖስ ዘመን አስቀድሞ ከ250 ዓክልበ. አካባቢ ጀምሮ ስለ ነበር፣ በአፊፋኖስ ዘመን ተጻፈ ለማለት ልዩ መግለጫዎች ይፈልጋል። እንዲሁም በታላቁ እስክንድር ዘመን (340 ዓክልበ ያሕል) የኢየሩሳሌም ቄሳውንት ከትንቢተ ዳንኤል ስለ ጠቀሱ እስክንድር ከተማቸውን አልፈረሰም የሚል ታሪክ በፍላቪዩስ ዮሴፉስ (100 ዓም ግድም) ጽሑፍ ውስጥ ይገኛል።

ትንቢተ ዳንኤል በዕብራይስጥና በአራማይስጥ ቋንቋዎች የተጻፈ መጽሐፍ ነው፡፡ መጽሐፉ በዕብራይስጥ ይጀምርና በምዕራፍ 2፡4 ላይ ወደ አራማይስጥ ቋንቋ ይቀየራል፤ በድጋሚ በምዕራፍ 8፡1 ላይ ወደ ዕብራይስጥ ቋንቋ ተመልሶ እስከ መጨረሻው በዚሁ ቋንቋ ይደመድማል፡፡ በእርግጥ አራማይስጥ በስደት የቆዩበት ቦታ ቋንቋ መሆኑ ሲነገር ዕብራይስጥ ደግሞ የስደተኞቹ የእስራኤላውያን ቋንቋ ነበር፡፡ ጸሐፊው በዕብራይስጥ መጻፍ ከጀመረ በኋላ በስደት ጊዜ የተወለዱ ብዙ እስራኤላውያን ከዕብራይስጥ ይልቅ የተሰደዱበት ቦታ ቋንቋ የሆነውን አራማይስጥ መረዳታቸው በመገንዘቡ ምክንያት ወጣት ስደተኞችንም ለመርዳት በማሰብ ጭምር በአራማይስጥ መጻፍ ጀመረ የሚል መላ ምት በአንዳንድ ሊቃውንት ቀርቧል፡፡

ከ40 ዓም እና 90 ዓም መካከል ጽሑፉ እጅግ እንደ ተለወጠ ሊታወቅ ይቻላል። ምክንያቱም ከዚያ አስቀድሞ የነበሩት ግሪክኛ (፸ ሊቃውንት) እና ከቁምራን ጥቅል ብራናዎች መካከል የተገኘው ዕብራይስጥ /አራማይስጥ ትርጉም ከለውጦቹ በፊት የነበረው አጻጻፍ ያሳያሉ። በ90 ዓም ግን በተለይ በአይሁዶች ረቢው አኪቫ በን ዮሴፍ ጥረት፣ የብሉይ ኪዳን ቃላት በመላው ተቀየሩ፤ በተለይም ትንቢተ ዳንኤል በዚያም ውስጥ በተለይ ምዕራፍ 11 እጅግ ተቀየሩ። በትንቢተ ዳንኤል ውስጥ ለውጦቹ ከግሪኩ በተለይ ስለ በዙ፣ በ140 ዓም ያሕል ጤዎዶትዮን የተባለ አንድ አይሁዳዊ መምኅር አዲስ ግሪክኛ ትርጉም ሠራ፤ ይህም ከአኪቫ ማሶራዊ ትርጉም ጋር ይስማማል። ዛሬውም በእንግሊዝኛም ሆነ በአብዛኞቹ ልሳናት የትንቢተ ዳንኤል ትርጉም የአኪቫን ማሶራዊ ዕብራይስጥ ትርጉም ይከተላል፤ ነገር ግን በመጀመርያ ክፍለ ዘመናት የኖሩት ክርስትያኖች ከጤዎዶትዮን በፊት የተገኘውን «ጥንታዊ ግሪክ ዳንኤል» ያንብቡ ነበር።

የመጽሐፉ ይዘት፣ ያጻጻፉ ስልት መለያየት፣ የተጻፈበት ቋንቋ ከአንድ በላይ መሆን፣ ያካተታቸው ታሪኮች ይዘት፣ የሕልሞችና ራእዮች ሁኔታ እንዲሁም የተጠቀመው የዘመን አቆጣጠር ሲታይ በአንድ ጸሐፊና በአንድ ወቅት የተጻፈ ነው ብሎ ለማመን ያስቸግራል፡፡ ምናልባት የታሪኩ ዋናው ክፍል ቀድሞ ተጽፎ በኋላ ሌሎች የቀድሞውን ጽሑፍ በመከለስ አዳዲስ ነገሮችን አካተው በድጋሚ ጽፈውት ሊሆን እንደሚችል ይታመናል፡፡ የመጽሐፉ ይዘት በምናይበት ጊዜ ሕልምና ራእይ፣ በደግና በክፉ መካከል የሚደረጉ ትግሎች፣ ምሳሌያዊ ቁጥሮች፣ ስለ ዓለም መጨረሻ ክንውኖች፣ የፍርድ ሂደቶች ከታሪካዊ ክስተቶች ጋር አጣምሮ የያዘ ነው፡፡ መጽሐፉ የጻፈው ወይንም የጻፉት ሰዎች ቅዱሳት መጻሕፍትን ያወቁና ያገናዘቡ እንደሆኑ ጽሑፉ ውስጥ ከተካተቱት ከቀድሞ የነቢያቶች፣ የጥበብና የኦሪት መጻሕፍት ጥቅሶች መረዳት ይቻላል፡፡

በአጠቃላይ በመጽሐፉ የመጀመሪያው ክፍል ውስጥ ልብ ሰቃይ የሆኑ የፍርድ ሂደቶችና እምነትን በመፈታተን ወደ ክህደት ሊመሩ የሚችሉ ክንውኖች ቢኖሩም የመጽሐፉ ዋና ገጸ ባሕርይ የሆኑት ዳንኤልና ሦስቱ ወዳጆቹ ግን በእግዚአብሔር ላይ ባላቸው የእምነታቸው ጽናት አሸናፊዎች ሆነው በመወጣት ነገሩን በድል ሲያጠናቅቁ ይታያል፡፡ የመጽሐፉ ሁለተኛው ክፍል ግን(ዳን 7-14) አብዛኛው ትኩረቱ ዳንኤል በሚያያቸው ራእዮችና መላእክቶች በሚሰጡት የራእዮቹ ትርጓሜ ላይ ነው፡፡

ዳንኤልና ሦስቱ ወዳጆቹ በስደት ወደ ባቢሎን ተማርከው ታዋቂና የንጉሥ አገልጋይ ሆኑ

[ለማስተካከል | ኮድ አርም]

በወቅቱ የባቢሎን ንጉሥ የነበረው ናቡከደነፆር አይሁዳውያን ብልኾችና ጠንካሮች እንደሆኑ ያውቅ ስለነበር በቤተ መንግሥቱ ውስጥ የሚያገለግሉት አይሁዳውያን ተመርጠው እንዲዘጋጁ አዘዘ፡፡ በዚህም መሠረት ዳንኤልና ሦስቱ ወዳጆቹ በባቢሎን ውስጥ እያሉ ከእስራኤል ምርኮኞች መካከል ተመርጠው ለሦስት ዓመት ከሠለጠኑ በኋላ በንጉሡ ፊት ቀርበው ሥራቸውን እንዲ ምሩ ተወሰነ(ዳን 1)፡፡ዳንኤልም ደስ የሚያሰኘው የንጉሡን ምግብ በመመገብና የወይን ጠጁንም በመጠጣት ራሱን ላለማርከስ ቁርጥ ውሳኔ በማድረግ የአትክልት ምግብ ብቻ ይመገብ ነበር፡፡ እግዚአብሔርም ለዳንኤልና ለሦስቱ ወዳጆቹ በማናቸውም ጥበብና ሥነ ጽሑፍ ዕውቀትና ማስተዋል ሰጣቸው፤ ዳንኤል ግን በተጨማሪ ራእይንና ሕልምን የመተርጐም ችሎታ ነበረው፡፡ በናቡከደነፆር ፊት ቀርበው ማገልገል ሲጀምሩም በማናቸውም ጥበብና ማስተዋል ንጉሡ ለሚያቀርበው ጥያቄና እንቆቅልሽ ሁሉ ፈጥኖ መልስ በመስጠት ረገድ በግዛቱ ካሉት ጠንቋዮችና አስማተኞች መካከል እነርሱ ዐሥር ጊዜ ብልጫ ያላቸው ሆነው ተገኙ፡፡ በዚህ ሁኔታ መጽሐፉ ገና ከጅምሩ ዳንኤልን በድሎትና በሥልጣን የማይበገር ጥበበኛ፣ ታማኝና የወገኖቹን ባህልና ሥርዓት ጠባቂ አድርጎ ያቀረበዋል፡፡ ይህ መሆኑ ለቀጣዩ ክፍል እጅግ በጣም አስፈላጊ ነው፡፡ በእርግጥ በቀጣዩ ክፍል ይህንን ጥበቡና ታማኝነቱ ወደ ላቀ ደረጃ እንደሚያደረሱትና ዝናውን የበለጠ የገነነ እንደሚያረጉት ያስገነዝባል፡፡

ቀጥሎም ዳንኤል ለንጉሥ ናቡከደነፆር የናቡከደነጾር የምስል ሕልምን ከነትርጓሜው ገለጠለት(ዳን 2)፡፡ ይህ ጥበብ የተሞላበት ድርጊቱ በንጉሡ ታላቅ የክብር ቦታ እንዲቀመጥ፣ ብዙ ስጦታዎች እንዲያገኝ፣ በባቢሎን ግዛቶችም ሁሉ ላይ የበላይ ገዥ እንዲሆንና በባቢሎንም ጠቢባን ሁሉ ላይ አለቃ እንዲሆን አደረገው፡፡ ከዚህ በኋላ ለዳንኤል ሦስቱ ወዳጆች የመጀመሪያው የመፈተኛ ጊዜ ይሆናል(ዳን 3)፡፡ በዚህ አስቸጋሪ የፈተና ጊዜ ሦስቱ የዳንኤል ጓደኞች ለወርቁ ምስል ባለመስገዳቸው ተከሰሱ፤ በሞት እንዲቀጡ ተፈረደባቸው፤ በመጨረሻ ግን በእምነታቸው ጽናት ምክንያት ታሪኩ ሙሉ በሙሉ ተቀይሮ ከእሳት ውስጥ ወጥተው ተሾሙ፡፡ ዳንኤል ሁለተኛውን የናቡከደነፆር ሕልም እንደ ተረጐመ፤ ናቡከደነፆርም ለእግዚአብሔር ምስጋና አቀረበ፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘ ሁኔታ እግዚአብሔር በሰጠው ብልኀት፣ዕውቀትና፣ ጥበብ በመመራት ዳንኤል ንጉሥ ቤልሻጻር ያየውን ምሥጢራዊ ጽሑፍ ነገር ግን ማናቸውም ጠቢባን አማካሪዎቹና አስማተኞቹ ሁሉ ሊተረጉሙት ያልቻሉትን ለንጉሡ ገለጠ፡፡ በዚህም ምክንያት የክብር ምልክት የሆነውን የወርቅ ሐብል በአንገቱ እንዲያደርጉለትና በመንግሥቱም ሥልጣን ሦስተኛውን ማዕረግ እንዲይዝ በዐዋጅ ተነገረ(ዳን 5)፡፡ በዚህ ምክንያት ዳንኤልና ሦስቱ ወዳጆቹ ባቢሎን(የዛሬዪቱ ኢራቅ) ውስጥ ትልቅ የክብር ቦታ ተቀዳጁ፡፡

የዳንኤልና ሦስቱ ወዳጆቹ ታማኝነታቸው ምስክር

[ለማስተካከል | ኮድ አርም]

በእግዚአብሔር ላይ የሚደረግ ታማኝነት የመጽሐፉ ዋና ትኩረት ስለሆነ ይህንን ታማኝነት ግልጽ በሆነና ትምህርት ሰጭ በሆነ መልኩ ተደጋግሞ ተገልጿል፡፡ ዳንኤልና ሦስቱ ወዳጆቹ ለእግዚአብሔርና ላደጉበት አይሁዳዊ ባህልና ሥርዓትፍጹም ታማኝ መሆናቸውን በተለያየ መልኩ ተገልጿል፡፡ ዳንኤልና ወዳጆቹ በንጉሡ ቤት በልዩ ሁኔታ የተዘጋ  ምግብና ወይን ጠጅ እየተመገቡና እየጠጡ እንዲያገለግሉ ቢፈቀድላቸውም መቀበል አልፈለጉም፡፡ የንጉሡን ምግብ በመመገብና የወይን ጠጁንም በመጠጣት ራሳቸውን ላለማርከስና አትክልት ብቻ እየተመገቡና ውሃ እየጠጡ ለመቆየት መምረጣቸውን ነው(ዳን 1፡8)፡፡ በእርግጥ በኦሪት ዘሌዋውያን ምዕራፍ 11 ላይ እግዚአብሔር ለሙሴና ለአሮን ለምግብነት መዋል ስለሚገባቸውና ስለሌለባቸው ወይም ስለ ረከሱ እንስሳትና አዕዋፋት በተመለከተ የአመጋገብ ሥርዓት ሲሰጥ ይታያል፡፡ ባቢሎናውያን ምንአልባት ከእነዚህ ከተከለከሉት እንስሳትና አዕዋፋት መካከል ውስጥ ይመገቡ ነበር፡፡ ዳንኤልና ወዳጆቹ ግን ለአይሁዳዊነት ባህልና ሥርዓት እንዲሁም ለእግዚአብሔር ሕግ ታማኝነታቸውና ታዛዥነታቸው የንጉሡን ምግብ ላለመብላት በመወሰን አሳይተዋል፡፡

ቀጥሎም ለእግዚአብሔር ታማኝነት የተገለጸው በሦስቱ የዳንኤል ወዳጆች ሲሆን ይህም ናቡከደነፆር ላቆመው የወርቅ ምስል አንሰግድም በማለታቸው ምክንያት በሚነደው የእሳት ነበልባል ውስጥ እስከመጣል መድረሳቸውን ነው፡፡ እነዚህ ሦስቱ የዳንኤል ወዳጆችም እኛ የምናገለግለው አምላክ ከዚህ ከሚነድደው ከእሳቱ ነበልባልም ሆነ ከአንተ እጅ ሊያድነን ይችላል፤ ንጉሥ ሆይ! እርሱ ሊያድነን ፈቃዱ ባይሆን እንኳ አማልክትህን እንደማናመልክና ላቆምኸው የወርቅ ምስል እንደማንሰግድ ዕወቅ በማለት ቈራጥነታቸውንና ታማኝነታቸውን ለእግዚአብሔር ገለጹ(ዳን 3፡17-18)፡፡ ታማኝነታቸውና ከእግዚአብሔር የተደረገላቸውን ጥበቃ ንጉሡን ጭምር ያስደነቀ እንደነበር ሲገልጽ አስረን በሚነደው የእሳት ነበልባል ውስጥ የጣልናቸው ሰዎች ሦስት ብቻ አልነበሩምን? እነሆ እኔ እሳቱ ምንም ሳይጐዳቸው ከእስራት ተፈትተው በነበልባሉ ውስጥ የሚመላለሱ አራት ሰዎች አያለሁ፤ አራተኛውም የአማልክትን ልጅ ይመስላል ይላል(ዳን 3፡24-25)፡፡ቀጥሎ የምናገኘው የዳንኤል መፈተንና ያሳየውን  ግንነት የተሞላበት ታማኝነቱን ነው፡፡ የንጉሥ ዳርዮስ መሳፍንት ወደ ንጉሡ በመሄድ ዳንኤል አንተን አያከብርህም፤ ፈርመህበት የወጣውንም ዐዋጅ በመጣስ በቀን ሦስት ጊዜ ወደ አምላኩ ይጸልያል ብለው በመክሰስና ንጉሥ ያስተላለፈው ዐዋጅ ወይም ትእዛዝ መለወጥ እንደማይቻል ለንጉሡ በማረጋገጥ በአንበሶች ጉድጓድ እንዲጣል አደረጉት(ዳን 6፡15-16)፡፡ ይህ ከመደረጉ በፊት ግን በድርጊቱ እጅግ በጣም ያዘነው ንጉሥ ዳርዮስ ዳንኤልን ሁልጊዜ በታማኝነት የምታገለግለው አምላክህ ያድንህ በማለት አበረታታው(ዳን 6፡16)፡፡ የታመኑትን ሁሌም የሚታደገው አምላክ ዳንኤልን በአንበሶች እንዲቦጫጨቅ አልፈቀደምና አንበሶቹ እንዳይጎዱኝ እግዚአብሔር መልአኩን ልኮ አፋቸውን ዘጋ፤ ይህንንም ያደረገው እኔ ንጹሕ መሆኔንና አንተንም አለመበደሌን ስላወቀ ነው በማለት በውሳኔው ተረብሾ እንቅልፍ አጥቶ ላደረው ለንጉሡ ይገልጽለታል(ዳን 6፡21)፡፡ በዳንኤል ምስክርነትና ባዳነው አምላክ የተደነቀው ንጉሥ ዳርዮስ በመንግሥቴ የሚኖር ሕዝብ ሁሉ የዳንኤልን አምላክ እንዲፈራና እንዲያከብር በዐዋጅ አዝዣለሁ፤ እርሱ ሕያውና ዘላለማዊ አምላክ ነው፤ እርሱ ዘላለማዊ ንጉሡ ነው፤ ለመንግሥቱም ፍጻሜ የለውም በማለት ለሕዝቡ ትእዛዝ አስተላለፈ(ዳን 6፡ 26-27)፡፡ በአጠቃላይ በዳንኤልና በሦስቱ ወዳጆቹ የተከናወኑት  ግንነት የተሞላባቸው ምስክርነቶች አይሁዳውያን ሃይማኖታቸው፣ ባህላቸው፣ ሥርዓቶቻቸው ጠብቀው ለእግዚአብሔር ታማኝ ሆነው ለማንኛውም አረማዊ ንጉሥ ሳይፈሩ፣ ሳይንበረከኩና በጥቅማጥቅምና በሥጋዊ ድሎት ሳይታለሉ መመስከርና በእምነታቸው መጽናት እንዳለባቸው የሚያሳይ ነው፡፡

ስለ ሙታን መነሣትና ስለ መጨረሻው ፍርድ

[ለማስተካከል | ኮድ አርም]

ብሉይ ኪዳን ውስጥ ከሞት በኋላ ስላለው ፍርድና የሕይወት ሁኔታ የሚገልጹ የመጽሐፍ ክፍሎች እጅግ በጣም ጥቂት ናቸው፡፡ ከእነዚህም ውስጥ ትንቢተ ዳንኤል ከሞት በኋላ ስለሚኖረው ፍርድና የእያንዳንዱ ሰው የመጨረሻ እጣ ፈንታ ምንም በማያሻማ ሁኔታ ስለሚገልጽ ከብሉይ ኪዳን መጻሕፍት እንደ ዋና መረጃ ሆኖ ይጠቀሳል፡፡ትንቢተ ዳንኤል አገላለጽ ዳግመኛ ሕይወት ወይም ትንሣኤ በምንልበት ጊዜ ከሞት በኋላ በነፍስ ብቻ ሳይሆን በሥጋና በነፍስ ሕይወት ማግኘትን ያመለክታል፡፡ በእርግጥ አንዳንድ መጻሕፍት ሰዎች ሥጋቸው በስብሶ መሬት ውስጥ እንደማይቀር፣ በሥጋ እንደሚነሡና ዘላለማዊ ሕይወት አግኝተው እንደሚኖሩ ያስገነዝባሉ(መዝ16፡9-11፤ ኢሳ 26፡19)፡፡ እንደ ትንቢተ ዳንኤል አገላለጽ የዓለም ፍጻሜ ከመሆኑ በፊት ሕዝቡን ሁሉ የሚፈታተንና ለሥቃይ የሚዳርግ በምድር ላይ ታላቅ የመከራ ጊዜ ይመጣል(ዳን 12፡1)፡፡ በምድር ላይ ምንም እንኳ አስቸጋሪ የሆነ የመከራ ጊዜ ቢከሰትም ስማቸው በእግዚአብሔር መጽሐፍ የተጻፉት ግን ይድናሉ(ዳን 12፡1)፡፡ እነዚህ በታማኝነት ጸንተው በመኖር የመከራ ጊዜን በብቃት የሚወጡትና ስማቸው በእግዚአብሔር መጽሐፍ የተጻፉት በፈተና ነጥረውና ጠርተው በመውጣታቸው እንከን የሌለባቸው ስለሚሆኑ ቢሞቱም ተነሥተው በመጨረሻው ቀን የክብር ድርሻቸውን እንደሚያገኙ መልአኩ ለዳንኤል ያረጋግጥለታል(ዳን 11፡35፤12፡ 10-13)፡፡ ስለዚህ አስቀድመው በሞት ተለይተው የነበሩት ተነሥተው እንደገና በሕይወት ይኖራሉ፤ ከእነርሱም እኩሌቶቹ የዘላለም ሕይወት አግኝተው ሲደሰቱ እኩሌቶቹ ለዘላለም በሐፍረትና በጉስቁልና ይሠቃያሉ(ዳን 12፡2)፡፡ የዘላለም ሕይወት አግኝተው ከሚደሰቱትም መካከል ውስጥ ጠቢባኖችና ብዙ ሰዎችን በማስተማርና ጥበባቸውን አገልግሎት ላይ በማዋል ሌሎችን ከክፉ መንገድ ወይም ከጥፋት ጐዳና ወደ ደግ ሥራ የመለሱ ሁሉ ብልጫ እንዳላቸው ይገልጻል(ዳን 12፡3 እና 10)፡፡

መላእክትና አገልግሎታቸው

[ለማስተካከል | ኮድ አርም]

መላእክት ተላላኪ መልእክተኞች፣ በፍጥረታቸው ረቂቃን የሆኑ፣ ብዛታቸው የማይቆጠር፣ ኃይላቸው ብርቱ፣ ቅዱሳን ጠባቂዎች፣ ስለ ታናናሾች በእግዚአብሔር ፊት የሚቆሙ አልፎ አልፎ ራሳቸውን በሰው መልክ የሚገልጹና እግዚአብሔርንም የሚያመሰግኑ መሆናቸው በቅዱስ መጽሐፍ ውስጥ በተለያየ መልኩ ተጠቅሶ እናገኘዋለን(ዘፍ 19፡1 እና 12፤ ኢዮ 1፡6፤ ዳን 8፡15-26፤ ኢሳ 6፤ ዘካ 14፡5፤ ማቴ 18፡10፤ ማቴ 22፡30፤ ማቴ 24፡36፤ ሉቃ 15፡10፤ ሉቃ 24፡39፤ ራእ 5፡11-12፤ ዕብ 1፡4)፡፡ በትንቢተ ዳንኤል ውስጥ ግን መላእክቶች ግልጽ በሆነ ሁናቴ በስማቸው እየተጠሩ የተለያዩ የአገልግሎት ተግባራት ሲወጡ ይታያል፡፡ ከእነዚህም ውስጥ የመጀመሪያው መላኩ ቅዱስ ገብርኤል ነው፡፡

መላኩ ገብርኤል ዳንኤል ወደነበረበት ቦታ በመድረስ ግራ የተጋባባቸውና መፍታት ያልቻላቸውን ራእዮች በመተንተን ያስረዳዋል (ዳን 8፡15-27፤ ዳን 9፡21-27)፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ዳንኤል ስለ እስራኤላውያን ኃጢአት እየተናዘዘ ምሕረትን ከእግዚአብሔር ሲለምን መላኩ ገብርኤል ወደ እርሱ በመቅረብ ገና መጸለይ ስትጀምር እግዚአብሔር ልመናህን ሰምቶአል፤ እርሱ ስለወደደህም የጸሎትህን መልስ ልነግርህ መጥቼአለሁ፤ እንግዲህ የራእዩን ትርጉም ስነግርህ በጥንቃቄ አድምጠኝ በማለት የእግዚአብሔር ተላላኪነቱና ራእይ ፈቺነቱ ይገልጻል(ዳን.9፡23)፡፡ በተጨማሪም መላኩ ገብርኤል እኔ ወደዚህ የመጣሁት የትንቢቱን ምስጢር እንድታውቅ ጥበብንና ማስተዋልን ልሰጥህ ነው በማለት ጥበብንና ማስተዋል እንዲሰጥ ከእግዚአብሔር ዘንድ የተላከ መሆኑን ይገልጻል(ዳን 9፡22)፡፡ ከዚህ የምንረዳው መላኩ ገብርኤል ከእግዚአብሔር ጋር ቀረቤታ እንዳለው፣ ሰዎች ግራ ተጋብተው ችግራቸውን ለእግዚአብሔር በጸሎት በሚገልጹበት ጊዜ የጸሎታቸውን ምላሽ በመያዝ በፍጥነት የሚደርስ፣ ራእዮችን በመፍታት ነገሮች ግልጽ የሚያደርግ ታማኝ መልእክተኛ ነው፡፡ ሌላው በትንቢተ ዳንኤል ውስጥ በስም የተጠቀሰውና ብዙ የአግልግሎት ተግባራት የሚፈጽመው መላኩ ቅዱስ ሚካኤል ነው፡፡ ዳንኤል በጤግሮስ ወንዝ አጠገብ በሐዘን ላይ ለሦስት ሳምንታት ሥጋም ሆነ ሌላ ምግብ ሳይበላ፣ የወይን ጠጅም ሳይጠጣና ቅባትም ሳይቀባ በቆየበት ጊዜ አስደናቂ የሆነ ራእይ አየ (ዳን 10፡2-8)፡፡ በዚህ ጊዜ ዳንኤል ኃይሉ ሁሉ ተሟጦ እጅግ በጣም ከመድከሙ የተነሣ መልኩ ተለዋውጦ ባየው ራእይ በመደንገጥ እንደ በድን ሆኖ መሬት ላይ ወደቀ፤ በፍርሃትም ተንቀጠቀጠ (ዳን 10፡9)፡፡ በዚህ ጊዜ በስም ያልተጠቀሰ መልአክ ወደ ዳንኤል ደርሶ ደጋግፎ በእጁና በእግሩ እንዲቆም ካደረገው በኋላ በእግዚአብሔር ዘንድ እጅግ የተወደድህ ዳንኤል ሆይ! እነሆ እኔ ወደ አንተ ተልኬ መጥቻለሁ፤ ባለህበት ጸጥ ብለህ ቁም፤ የምነግርህም ጸጥ ብለህ አስተውል በማለት ካበረታታው በኋላ የሚነግረውን በጥንቃቄና በማስተዋል እንዲሰማው ያስገነዝበዋል (ዳን.10፡11)፡፡ በመላኩ ንግግር ውስጥ በፋርስ ብቸኛ መሆኔን አይቶ ከመላእክት አለቆች አንዱ የሆነው ሚካኤል ሊረዳኝ መጣ ካለ በኋላ በድጋሚ በንግግሩ መጨረሻ ላይ የእስራኤል ጠባቂ መልአክ ከሆነው ከሚካኤል በቀር እኔን የሚረዳ የለም በማለት ይደመድማል (ዳን 10፡13 እና 21)፡፡ ከዚህ የምንረዳው መላኩ ሚካኤል የመላእክቶች አለቃ፣ የእግዚአብሔር ሕዝብ ብርቱ ጠባቂ፣ የእግዚአብሔር ታማኞች በብቸኝነት ኑሮ በተጎሳቈሉ ጊዜ ፈጥኖ የሚደርስና የሚረዳ መልእክተኛ እንደሆነ ነው፡፡ በተጨማሪም መላኩ ሚካኤል የዓለም ፍጻሜ በሚሆንበት ጊዜ እንደሚገለጥ ሲናገር ሕዝብህን የሚጠብቀው ታላቁ መልአክ ሚካኤል በዚያን ጊዜ ይገለጣል ይላል (ዳን 12፡1)፡

በአዲስ ኪዳን ውስጥ ተጠቅሶ

[ለማስተካከል | ኮድ አርም]

አዲስ ኪዳን ጸሐፊዎች ውስጥ ትንቢተ ዳንኤልን በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ በሰፊው የጠቀሰው ዮሐንስ ሲሆን ይህም በራእይ ውስጥ ነው፡፡ ቅዱስ ዮሐንስ "አንድ አውሬ ከባሕር ሲወጣ አየሁ" በማለት ስለ አውሬው የሚዘረዝረውን ዳንኤል 7 ላይ ከተገለጸው አውሬ ጋር እጅግ በጣም ተቀራራቢ የሆነ ተመሳሳይነት አለው(ራእ 13)፡፡ በዮሐንስ ራእይ እንደ መለኮታዊ ተዋጊ፣ ትክክለኛ ፈራጅ፣ ዐይኖቹ በእሳት ነበልባል የተመሰሉት፣ በደም የተነከረ ልብስ የለበሰው፣ ስሙም "የእግዚአብሔር ቃል" ተብሎ የተጠራውና ክፋትን ሁሉ ድል ያደረገው በነጭ ፈረስ ላይ የተቀመጠ ፈረሰኛ ተጠቅሷል፡፡ በትንቢተ ዳንኤል ደግሞ "የሰውን ልጅ የሚመስል በሰማይ ደመና ተከብቦ ሲመጣ አየሁ" ይላል፡፡ እነዚህ ሁለቱ ገጸ ባሕርያት ተመሳሳይነትና ተዛማጅነት እንዳላቸው መረዳት አያዳግትም(ራእ 19፡ 11-21፤ ዳን 7፡ 13)፡፡ በተጨማሪም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በተደጋጋሚ ራሱን "የሰው ልጅ" ብሎ ይጠራ እንደነበርና ይህም የሰው ልጅ የሚለው ቃል በትንቢተ ዳንኤል ውስጥ ቀድሞውኑ ተገልጾ እንደነበር ይታወቃል፡፡ በአጠቃላይ የዮሐንስ ራእይ በብዙ መልኩ ከትንቢተ ዳንኤል ጋር ተመሳሳይነት ስላለው ሳቦቹም ከዛው ጋር የተወራረሱ ስለሆኑ ጸሐፊው ትንቢተ ዳንኤልን እንዳነበበውና የሚጽፈውም ሁሉ በቂ የሆነ የትንቢተ ዳንኤል ተወራራሽ  ሳባች እንደተጠቀመ መረዳት ይቻላል፡፡

የእግዚአብሔር መንግሥት ከዓለም መንግሥታት ጋር ሲወዳደር

[ለማስተካከል | ኮድ አርም]

ትንቢተ ዳንኤል እነዚህ ኃያላን መንግሥታት በመጥቀስና ከእግዚአብሔር መንግሥት ጋር በማወዳደር ኃያሉና እውነተኛው መንግሥት የትኛው እንደሆነ አንባቢው እንዲረዳና የራሱን ድምዳሜ ላይ እንዲደርስ ያደርጋል፡፡ ለምሳሌ ለዳንኤል የተገለጠለት ስለ አራቱ አውሬዎችና ለዘላለም ሕያው ሆኖ ስለሚኖረው ራእይ ይህንኑ የዓለም መንግሥታትና የእግዚአብሔር መንግሥት የማወዳደር ሁኔታ ይንጸባረቃል (ዳን 7)፡፡ በዚህ ራእይ እንደምንረዳው ከአራቱ ማእዘናት የተነሣውነፋስ ታላቁን ባሕር ባናወጠው ጊዜ አራት የተለያዩ ታላላቅ አውሬዎች ከባሕሩ ወጡ። እነዚህም በአንበሳ፣ በድብ፣ በነብርና አንድ ኃይለኛ፣ አስቀያሚና አስፈሪ በሆነ እንስሳቶች የተመሰሉ ነበሩ። ይችም አንበሣ የንሥር ክንፎች የነበራትና የንሥር ክንፎቿም የሚነቀሉባት አውሬ ናት። አራተኛዋም አስቀያሚዋ አውሬ ፲ ቀንዶች (አለቆች) አሏት፤ ከነዚህም መካከል ሌላ ትንሽ ቀንድ ለትወሰነ ጊዜ በትዕቢት እየተናገረ ዓለሙን ይጨቆናል። ከትግሎች ሁሉ በኋላ በመጨረሻም እነዚህ አውሬዎች ሥልጣናቸውን ተነጠቁ። በሌላ መልኩ የሰውን ልጅ የሚመስል በሰማይ ደመና ተከብቦ ሲመጣ ታየ፡፡ ይህ በሰው ልጅ የተመሰለው ግን ለዘላለም ሕያው ወደሆነው ፊት አቀረቡት፡፡ በልዩ ልዩ አገር የሚኖሩ ሕዝቦችና ልዩ ልዩ ቋንቋ የሚናገሩ ነገዶች ያገለግሉት ዘንድ ሥልጣን፣ ክብርና ኀይል ተሰጠው፤ ሥልጣኑ ለዘላለማዊ ነው፤ ለመንግሥቱም ፍጻሜ የለውም(ዳን 7፡1-14)፡፡

በምዕራፍ 8 ስለ «ፍጻሜ ዘመን» (8፡17) የሆነ ሌላ ራዕይ ይታያል። ይህ የአውራ በግና አውራ ፍየል ትርዒት ነው። ፍየሉ በምድር ስፋት ሁሉ ምድርን ሳይነካ አውራ በግ በኤላም መታ፣ ፪ ቀንዶቹን ሰበረ። መልዓኩ እንደሚያስረዳው የበጉ ፪ ቀንዶች መታወቂያ የማዴ (ሜዶን)ና የፋርስ ነገሥታት ሲሆኑ፣ የፍየሉም መታወቂያ የያዋን (ግሪክ ወይም ምዕራባውያን) ንጉሥ ነው። ከዚህ ትግል በኋላ፣ ፍየሉ ይታበያል፣ አንድያ ቀንዱ ተነቅሎ አራት ቀንዶች ይከተላሉ፤ ከነዚህም አራት ቀንዶች መካከል ትንሽ ቀንድ ይነሣል፤ ትንሹም ቀንድ እንደ ምዕራፍ 7 ለተወሰነ ጊዜ ዓለሙን በጭካኔ የሚገዛው ነው።

በመጨረሻም ከዳን 10-11 እንደምንረዳው ሌሎችም ታላላቅ «የስሜን» ነገሥታት የተባሉትም ተነሥተው ለጥቂት ጊዜያት ከገዙ በኋላ ይወድቃሉ። ታላላቅ ከተባሉትም ውስጥ መጨረሻው ክፉ ንጉሥ የኤዶምሞአብአሞን፤ የግብጽ፣ የሊቢያና የኢትዮጵያ ሀብቶች ወይንም ሰዎች ይበዝብዛል (ዳን 11፡43)። (በዕብራይስጥ ትርጉም፣ እነዚህ መጨረሻ ሦስቱ የካም ልጆች ምጽራይምፉጥኩሽ ስሞች ናቸው። በአራተኛው ልጅ በከነዓን ፈንታ ግን የአብርሃም ዘሮች የነበሩት «ኤዶም፣ ሞአብና አሞን» አለው።) ይህ ስስታም ንጉሥ በመጨረሻው ይጠፋል፤ የሚረዳውም አይገኝም (ዳን 11፡45)። ከተወሰኑት ቀኖች ቁጥር በኋላ ግን፣ የእግዚአብሔር መንግሥትና በታማኝነት የሚኖሩት ሕዝቦቹ ጸንተው ይኖራሉ። ቢሞቱም እንኳ በመጨረሻው ቀን በሙታን ትንሳኤ የክብር ድርሻቸውን ያገኛሉ (ዳን 12)።

ሌላው በዳንኤል ከተተረጐመው የመጀመሪያው የንጉሥ ናቡከደነፆር ሕልም (ዳን 2) እንደምንረዳው በዓለም ላይ ኃያላን የተባሉና በወርቅ፣ በብር፣ በነሐስና በብረት የተመሰሉ አራት መንግሥታት ይነሣሉ። መጀመርያውም ባቢሎን መሆኑን ሲነገር፣ በተለመደው የተረፉት ፋርስ፣ ግሪክ እና የሮሜ መንግሥት ትንቢት እንደ ነበሩ ይታመናል። የእነዚህም ሕልሞች ፍቺ እንደሚያስረዱት ለናቡከደነፆር የሰማይ አምላክ መንግሥትንና ኃይልን፣ ሥልጣንና ክብርን እንደሰጠውና በሕልሙ ያየውን የወርቁ ራስ እንደሆነ ዳንኤል ያረጋግጥለታል (ዳን 2፡38)። ቀጥሎም ሌሎች ሦስት መንግሥታት እንደሚነሡ ከገለጸ በኋላ በነሐስና በብረት የተመሰሉት ሦስተኛውና አራተኛውን እጅግ በጣም ኃያላን ዓለምን ለመግዛትና ሁሉንም ነገር ለመሰባበርና ለማንኮታኮት የሚችሉ እንደሚሆኑ ያስገነዝባል። ነገር ግን በእነዚያም ነገሥታት ዘመን የሰማይ አምላክ ፈጽሞ የማይፈርስና ግዛቱም በሌላ ሕዝብ የማይደፈር መንግሥትን ይመሠርታል፤ ይህ መንግሥት ሌሎችን መንግሥታት እስከ መጨረሻው ያጠፋቸዋል፤ እርሱ ግን ለዘላለም ጸንቶ ይኖራል (2፡ 44-45)።