Jump to content

ፋሲለደስ

ከውክፔዲያ
(ከአፄ ፋሲል የተዛወረ)

==

ዓፄ ፋሲለደስ
የፋሲል ምስል፣ ኡራ ኪዳነ ምህረት
የፋሲል ምስል፣ ኡራ ኪዳነ ምህረት
ንጉሠ ነገሥት ዘኢትዮጵያ
ግዛት ከ1632 እስከ 1667 እ.ኤ.አ.
ቀዳሚ ዓፄ ሱስንዮስ
ተከታይ ቀዳማዊ ዓፄ ዮሐንስ
ሙሉ ስም ዓለም ሰገድ (የዙፋን ስም)
ሥርወ-መንግሥት ሰሎሞን
አባት ዓፄ ሱስንዮስ
እናት እቴጌ ስልጣን ሞገስ
የተወለዱት 1603 እ.ኤ.አ.
የሞቱት 1667 እ.ኤ.አ. በአዘዞ
የተቀበሩት ቅዱስ እስጢፋኖስ ገዳምደጋ ደሴት
ሀይማኖት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ክርስትና

==


ዓፄ ፋሲለደስ ወይም ዓፄ ፋሲል (የዙፋን ስማቸው ዓለም ሰገድ) ከአባታቸው አፄ ሱሰኒዮስ እና ከእናታቸው ልዕልት ስልጣነ ሞገስ በሸዋ ክፍለሀገር ቡልጋ መገዘዝ ፣ ህዳር 10፣ 1603 (እ.ኤ.አ) ተወለዱ። የነገሱበትም ዘመን ከ1632 እስከ ጥቅምት 18, 1667 (እ.ኤ.አ) ነበር።

ስረፀ ክርስቶስ በተመራው አመፅ ምክንያት በ1630 ፋሲለደስ ለንግስና ቢበቃም፣ ዘውዱን ግን እስከ 1632 አልጫነም ነበር። ሲመተ ንግስናው በ1632 እንደተገባደደ የመጀመሪያው ስራው የተዋህዶ ቤ/ክርስቲያንን የቀድሞው ቁመና መመለስና የካቶሊኮችን መሬት በመቀማት ከደንካዝ በማባረር በፍሪሞና እንዲወሰኑ ማድረግ ነበር። ወዲያውም በማከታተል ከግብፅ አገር አዲስ ጳጳስ እንዲላክለት በማድረግ በአባቱ ዘመን እንዲደበዝዝ ተደርጎ የነበረውን የግብፅና ኢትዮጵያ አብያተ ክርስቲያናት ግንኙነት እንዲጸና አደረገ። በኬኒያ የሚገኘው የሞምባሳ ወደብ በፖርቱጋሎች መደብደቡን ሲሰማ፣ የሮማው ፓፓ ከበስትጀርባው ያለበት ሴራ ነው በማለት በምድሩ የነበሩትን የካቶሊክ ጀስዊቶች በመሰብሰብ አባረራቸው።

ፋሲል ግምብፋሲል ግቢ

ጎንደር ከተማ

[ለማስተካከል | ኮድ አርም]

ፋሲለደስ የጎንደር ከተማን በ1636 የኢትዮጵያም ዋና ከተማ አድርጎ እንደቆረቆራት ይታመናል።[1] ከሱ በፊት በአካባቢው ከተማ እንደነበር ወይም እንዳልነበር በታሪክ የተገኘ ማስርጃ እስካሁን የለም። አከታትሎም የፋሲል ግቢን44ቱ ታቦታት ተብለው የሚታወቁትን የጎንደር ከተማ አብያተ ክርስቲያናት መሰረት ጣለ። በአፄ ፋሲል ከተመሰረቱት ታዋቂወቹ 44 አብያተ ክርስቲያናት፣ ታዋቂወቹ አደባባይ እየሱስአደባባይ ተክለ ሃይማኖትአጣጣሚ ሚካኤልግምጃቤት ማራያምፊት ሚካኤል፣ እና ፊት አቦ ይገኙበታል።[2] ያለመታከትም 7 የድንጋይ ድልድዮችን በማሰራት እስካሁን ድረስ ስሙ ሲጠራ ይኖራል። አልፎም በግራኝ አህመድ ዘመን በእሳት ጋይቶ የነበረችውን አክሱም ፂዮን በአዲስ መሰረት እንደገና ማሰራት ችሎአል።[3]

ፋሲለደስ በዘመኑ እጅግ ተወዳጅ ንጉስ ቢሆንም አመጽ መነሳቱ አልቀረም። በላስታ ለምሳሌ በ1637 መልክዓ ክርስቶስ በተባለ ሰው መሪነት ጦርነት ተነስቶ አፄ ፋሲልን ስጋት ላይ ቢጥልም በሚቀጥለው አመት በተደረገው ጦርነት አመፁ ሊገታ ችሎአል።[4]

ፋሲለደስ ፖርቱጋሎችን ቢያባርርም ከውጭው አለም ጋር ብዙ ግንኙነት ያደርግ ነበር። ለምሳሌ በ1664-5 የህንድ ንጉስ አውራንግዘብ ሲነግስ መልካም ምኞትን በመልክተኞቹ ለሙግሃሉ መሪ ልኮ ነበር።

በ1666 ልጁ ዳዊት ሲያምጽ፣ ወህኒ ተብሎ ወደሚታወቀው አገር በግዞት ልኮት ነበር። ይህም ከጥንቶቹ የኢትዮጵያውን ነገሥት ተፎካካሪያቸውን ወደ አምባ ግሽን በግዞት እንደሚልኩት ስርዓት ነበር።

የፋሲል እረፍት

[ለማስተካከል | ኮድ አርም]

አፄ ፋሲል አዘዞ ተብላ በምትታወቀው ከጎንደር ከተማ 5 ማይል ርቃ በምትገኘው ከተማ ጥቅምት18፣1667 እ.ኤ.አ. (ጥቅምት 10፣ 1660) ከዚህ አለም በሞት ተለዩ። አሟሟታቸውንም፣ በጊዜው በህዝቡ ዘንድ የነበራቸውን ተቀባይነት በሚያንጸባርቅ መልኩ፣ የዜና መዋዕል ዘጋቢያቸው እንዲህ ሲል ይተርካል፡

ጥቅምት ፰፣ እሁድ ዕለት፣ ፫ ሰዓት ላይ፣ [የፀሐይ] ጥላ በ፫ ጫማ ሲሰፈር፣ ለሰው ሁሉ እንደሆነ፣ ንጉሳችን አዲያም ሰገድ ድንገት ታመመ። በዚህ ጊዜ ታላቅ ሀዘን ተነሳ[...]ለሚቀጥሉት ሁለት ቀናት ምግብም ሆነ መጠጥ ሳያስብ[...] የብር ከበሮወችን እያፈረሰ፣ የወርቅ ስለቶችን አፎታቸውንም እየቆራረጠ የቤተክርስቲያን ማገልገልግያ አደረጋቸው። በዚህ ጊዜ በሁሉ ዘንድ እንባና ለቅሶ ሆነ [...]ሁሉም እንደሚያውቀው ንጉሳችን ከባህር አሸዋ በሚበዛ መልካም ተግባሩ ሁሉንም መልሶ ገንብቶ ነበርና[...]የሁሉም እምነት ንጉሳችን አለም ሰገድ ሲሞት ምድርና ሰማይ እንደሚንቀጠቀጡ፣ መሬት እንደሚናወጥ፣ ጠላትም በላያችን ሰልጥኖ አለቃችን እንደሚሆን ነበርና።
ማክሰኞ፣ የፀሐይ ጥላ በ4ጫማ ሲሰፈር፣ ከ3 ሰዓት በኋላ ንጉሳችን አረፈ...
አይ ጉድ! መልካም የሚናገረው አፉ ተዘጋ፣ ለዛ ያላቸው ቃላትን የሚያፈሰው ሽቶ ምላሱ እንዲሁ። ሐዘንና ለቅሶ ለዚህ ለምለም ተክል፣ አለፈ! [...] ምን እንላለን? የሆነው ሆኗል! አንት መልካም መዓዛ ያለህ ያገራችን አበባ! እንደ ተራ ነገር ትጠፋ? ነቢዩ
እንዳለ "ህይወት ኖሮት ሞትን የማያይ ማን ሰው አለ?"[5]

አስከሬናቸውም የአገሪቱ መላ ህዝብ ባዘነበት ሁኔታ በቅዱስ እስጢፋኖስ ገዳም፣ ጣና ሃይቅ ውስጥ ደጋ ደሴት ተብላ በምትታወቀው ደሴት የዘላለም እረፍት አገኘ። መቃብራቸውም ውስጥ ያንድ ትንሽ ህፃን አስክሬን አብሮ ይገኛል። ይሄውም ልጃቸው ሲሆን የወደፊቱ ንጉስ ለመሆን እጩ ነበር። ነገር ግን አዲሱን ንጉስ የመጣው ህዝብ ብዛት ሲተራመስ ድንገት ተጠቅጥቆ ለሞት በቃ።[6]

የፋሲለደስ ቅሪት፣ ደጋ እስጢፋኖስደጋ ደሴት [7]
  1. ^ Solomon Getamun, History of the City of Gondar (Africa World Press, 2005), pp.1-4
  2. ^ Getamun, City of Gondar, p. 5
  3. ^ Richard Pankhurst, Economic History of Ethiopia (Addis Ababa: Haile Selassie University Press, 1968), pp. 297f
  4. ^ James Bruce, Travels to Discover the Source of the Nile (1805 edition), vol. 3, pp. 435-437
  5. ^ የአጼ ፋሲለደስ ዜና መዋዕል
  6. ^ Nathaniel T. Kenney, "Ethiopian Adventure", National Geographic, 127 (1965), p.557.
  7. ^ Hespeler-Boultbee, John Jeremey, A Story In Stones: Portugal's Influence on Culture and Architecture in the Highlands of Ethiopia 1493-1693, CCB Publishing, British Columbia, 2011, page 101