ጎንደር ከተማ
የጎንደር ከተማ ታሪክ
ጎንደር ከ1628 ዓ ም ጀምሮ ለ200 ዓመታት የአፄወች መናገሻ በመሆኗ የምትታወቅ የዓለም ታዋቂ የታሪክ ተመራማሪወችን የምትስብ ውብ ከተማ ናት።
የዘመኑ አፄዎች የገነቧቸው ቤተ መንግስቶችና አብያተ ክርስቲያናት (ፋሲል ግንብ፣ የጉዝራ፣ ጎመንጌ- አዘዞ ገነተ እየሱስ፣ ጎርጎራ ማንዴ ወዘተ) የከተማዋንና የኢትዮጵያን ታሪክ ለዓለም ጥሩ ገፅታ ለመሆናቸው ከተለያዩ ክፍለዓለማት እንደ ጎርፍ ለጉብኝትና ታሪክን ለመቃኘት የሚተመውን ለአብነት መጥቀሳችን ሁላችንም ያስማማናል።
ፋሽስት ጣሊያን ኢትዮጵያን ከወረረ በኋላ የኢትዮጵያ ሕዝብ በአርበኝነት በረሀ ሲወርድ ያኔ ነበር የጣሊያን ወራሪው ሀይል ሕዝብን በማፈናቀል መሬትን መንጠቅ የጀመረው (see picture of Italian General addressing his army on top of Fasil Castle) ።
ለአብነት የጎንደር ሲኒማ ቤት በፋሽስት ጣሊያን ከመሰራቱ በፊት እርስትነቱ የአቶ መንክር ተገኘ የተሰኙ በዚያን ዘመን ጎንደር ከተማ ውስጥ በጣም የላቁና የመጠቁ ነገረ ፈጅ ወይንም ጠበቃ ነበሩ።
በዚያን ዘመን የህግ ባለሙያ ወይንም ጠበቃ ነበር ወይ ለምትሉ? በሀገራችን በዘመናዊ ትምህርት ቤት ባይማሩም ከቤተክህነት ትምህርትን የቀሰሙና ጥሩ አንደበተ ርህቱ የሆኑ ሰወች በጠበቃነት ተሰማርተው ይሰሩ ነበር።
ይህ ደግሞ በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ቀደምት ጥንታዊ ግሪካዊያንም በድሮ ዘመን የአቴንስ ጸሐፊዎችና ጥሩ ተናጋሪወች በጠበቃነት ያገለግሉ እንደነበር የታሪክ ድርሳናት ያመለክታሉ ።
ጎንደርም አቶ መንክር ተገኘ ስመ ጥር ጠበቃ እንደነበሩ የከተማዋ ታሪክ አዋቂወች ይናገራሉ።
በጣሊያን ወረራ ጊዜም አንዳድ የአካባቢው ነዋሪወችም አርበኞችን በማሳፈንና በማስገደል ከጣሊያን ጎን የቆሙትን ባንዳ ተብለው እንደሚጠሩ ታሪክ ያወሳል።
ወደ ተነሳንበት ጉዳይ እንመለስና ጣሊያን ጎንደርን ማዕከል ለማድረግ በማለም
በከተማዋ ውስጥ 352 ዛሬ የምናያቸውና ጣሊያን የሰራቸው ብለን የምንጠራቸውን ህንፃወችን ገነባ።
እነኝህ ህንፃወች በአብላጫው ፒያሳ፣ጨዋ ሰፈር፣ አራተኛ ፎቅ፣ ቀበሌ 21 እንዲሁም የድሮው አገር አስተዳደርና ክፍተኛ ፍርድ ቤት አሁንም ግልጋሎት የሚሰጡትን እናያለን።
ፒያሳን የንግድ መደብሮች፣የመዝናኛ ካፌና ፓርክ፣ሲኒማ ቤቱንና ባሩ፣ ምግብ ቤቶች ጣሊያኖች ለወታደሮቻቸውና ለጣሊያን ሲቪሊያን መገልገያ መመስረታቸውና ግልጋሎትም እነደሰጡ የሚጠቁሙት የአሁኑን
1- ቋራ ሆቴል በድሮ አጠራሩ (Grand Bar) ሲመሰርቱ፣
2- ጣሊያኖች አሊቤሮጎ ቻው ጣሊያን ሲወጣ እቴጌ መነን በኋላ ደግሞ ተራራ ሆቴል የተባለውን ያስታውሰናል።
ሌላው ፒያሳወች ስንቆፋፍር አንድ ያገኘነው መረጃ ቅዱስ ዮሀንስ የድሮው የጎንደር ፓሊስ ማስልጠኛ ወደ ልደታ አካባቢ ሮም ጣሊያን ድረስ የሚሰማ የአጭር ሞገድ ሬዲዮ ከጎንደር ተነቅሎ ወደ ሱዳን የሄደውና ኡምንድሩማን ሬዲዮ SUDAN RADIO OMDURMAN በመባል ካርቱም ላይ ግልጋሎት የሚሰጠው ከጎንደር የተሰረቀ እንደሆነ መረጃወች አሉ።
–ወደ ኦቶ ባሮኮ መውረጃ ቅዱስ ገብረዓል ጋራጅ ወይንም ዮሴፍ ጋራጅ በመባል የሚታወቀው ደግሞ የጣሊያኖች የጦር አዛዥ መኖሪያ እንደነበርም ለማወቅ ችለናል።
— ጣሊያን ከወጣ በኋላ የአሁኑን ቋራ ሆቴል አቶ ጌጡ ልዋጥህ Grand Bar የሚባለውን ወደ ልዑል መኮንን ሆቴል ብለው ቀይረው ግልጋሎት ይሰጡ ነበር
–ጣሊያን ከለቀቀ ማግስት Albergo Chawን በማደስ እቴጌ መነን ሆቴል (see Logo)ይመልከቱ ብለው እንደገና የከፈቱት የጃንሆይ ልጅ ልዕል ተናኘ ወርቅና ቡስኪ የተባለ ጣሊያን በጋራ ነበር በኋላም ተራራ ሆቴል ተብሎ መንግስት የወረሰው
–ጣሊያን ከተባረረ በኋላ ሲኒማ ቤቱንና ባሩን ደግሞ የያዘው Yannis የተባለ የግሪክና የኢትዮጵያ ክልስ እንደነበር የሲኒማው ማሳያ ሞተር በኢጅነርነት የሚሰሩ የነበሩት አቶ ተካቦ የነ ዮሀንስ እና ታፈረ አባት ነበሩ
ድህረ ጣሊያንስ ጎንደር ምን ትመስል እንደነበር በስሱ እንቃኝ!
ብዙ መረጃወች እንደሚያመለክቱት በ 1933 ዓ/ም ወይንም እንደ ፈረንጆቹ የጊዜ ቀመር በ1941 ዓ/ም ጦርነቱ ከተጠቃለለ በኋላ የወጣው የጠላት ጦር ከኢትዮጵያ ከወጣ በኋላ በድምሩ 130,000 (አንድ መቶ ሠላሳ ሺህ) ጣሊያኖች ኢትዮጵያ ውስጥ እንደነበሩ
ብዙ የታሪክ መዛግብት ይጠቁማሉ።
ከእነኚህ 130,000 ነጭ ጣሊያኖች ውስጥ 70,000 የጦር እስረኞችና 60000 ደግሞ ሲሺሊያን ነበሩ።
የእንግሊዝ መንግስት ቀን ተሌት አፄ ኋይለ ሥላሴን ጣሊያኖች ከኢትዮጵያ አንድም ሳይቀሩ ሙልጭ ብለው እንዲወጡ ተፅእኖ ቢፈጥሩም በንጉሡ ዘንድ የእንግሊዞች ግፊትተቀባይነት አለገኘም።
የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥትና በዙሪያቸው ወይንም በአካባቢያቸው በስልጣን እርከን ውስጥ የነበሩ መሳፍንቶችና አርበኞች ቢያንስ አንዳንዶቹ በተለይም የእጅ ሙያ ያላቸው ጣሊያኖች እንዲቆዩ ፍላጎታቸውን በግልፅ ማሳየት ጀመሩ።
ከሁሉም በላይ የቴክኒሻኖች አስፈላጊነታቸው በጣም ሰፊ ስለነበር እነኝህ ጣሊያኖች የመጓጓዣ ተሽከርካሪዎችን፣ የህንፃ ስራወች ጆሜትሪ፣ የመኪና ጥገና በሆስፒታሎች ለማገዝ እና ብዙ ሥራዎችን ለማከናወን ያገለግላሉ በሚል እምነት ነበር ብዙወቹ በፍላጎታቸው ኢትዮጵያ ውስጥ የቀሩት።
በዚህ ምክንያት ጎንደር ውስጥም የተወሰኑ ጣሊያኖች ነበሩ። ሥራም ሳይንቁ ህዝቡን መስለውና ተመሳስለው ኑሮ ጀመሩ።
ለምሳሌ ያህል ብልኮ ከቀድሞው ወወክማ YMCA ፊት ለፊት ከአቶ ደርበው ቡና ቤት ጎን ጎሚስታ ነበር ባለቤቱ ጣሊያናዊ እርጅና ሲጫጫነው አርበኞች አደባባይን እንድ ተጠለፈ አውሮፕላን በቅጠል ብጣሽ ቆርጦ እንደ ጭራ ይጠቀም ነበር።
ወደመጨረሻው አካባቢ አቶ ሰጠኝ የተባሉ የጎንደር ተወላጅ እዚያው ይሰሩ የነበሩ በባለቤትነት የያዙት ይመስለናል። ሁላችሁም እንደምታውቁት ፒያሳወች ወደ ብልኮ መሄድ ስለሚከብደን:-)
ሌላው ቢጋ የተሰኘ ጣሊያናዊ ሲትሮን Citroën የፈረንሳይ መኪና በመጠቀም ነበር ፍራፍሬና ወተት ለታላልቅ ሆቴሎችና ግሮሰሪ መደብሮች እንዲሁም ለባለ ፀጋ ጎንደሬወች ከአባሳሙዔል እርሻ በማጓጓዝ ያከፋፍል ነበር።
ጣሊያን ልክ ሲወጣ በዚይን ዘመን አባባል ጎንደርን በአገረ ገዥነት ከደርግ በኋላ ደግሞ አስትዳዳሪ ነው የሚባለው አገረ ገዥ የነበሩት የንጉሡ ልጅ አልጋ ወራሽ እንደነበሩ ይነገራል።
በዚህ ጊዜ ጎንደር ምንም ዓይነት የወታደር ባጀት ስላልነበረው አልጋ ወራሽ የጎንደር ነጋዴወች ለመንግስት ብድር እንዲያበድሩ ይጠይቁ ነበር።
በዚያን ጊዜ ነበር በጊዜው የታወቁት አዲስ ዓለም የሚኖሩት የጎንደር ቱጃር መረቀኔ መሐመድ 30,000 ጠገራ ብር ወይንም ማርትሬዛ ለመንግስት ያበደሩት። መረቀኔ መሐመድ በዚህ አሳቢነታቸውና ሀገር ወዳድነታቸው በከተማው በነበሩ ጠጅ ቤቶች ማታ ማታ መረዋ ድምጥ ያላቸው የጎንደር ሊቀ መኳሶች እንዲህ እያሉ ይገጥሙ ነበር
….የሀበሻ ወታደር የሚበላው አጥቶ
….መርቀኔ መሐመድ አበላወ ሸምቶ
እየተባለላቸው ላሳቢነታቸውና ለሀገር ወዳድነታቸው በግጥም ይወደሱና ይመሰገኑና ነበር።
ለሀገር መስራት ሁሌም ያስመሰግናልና።
አሁንም ፒያሳወች እዚያው ፒያሳ ላይ እናጠንጥንና የአሁኑ ቋራ ሆቴል ጣሊያን እንደወጣ አቶ ጌጡ ልዋጥህ Grand Barን አድሰው ግልጋሎት መስጠት ከጀመሩ በኋላ ይህ ሆቴል በጠላት የተገነባ ስለሆነ ወደ መንግስት ይዞታ መዛወር አለበት በማለት አገረ ገዡ በንጉሡ ልጅ አልጋ ወራሽ ትእዛዝ ተወስዶ ለወንድማቸው ለልዑል መኮንን ተሰጠ።
ከዚያም ልዑል መኮንን ሲያርፉ ሆቴሉ ለረዥም ጊዜ ተዘግቶ ከኖረ በኋላ ፊታውራሪ ተስፋየ አስናቀ እና አቶ ኪዳኔ በሽርክነት አድሰው እንደገና ከፈቱት። ምንም እንኳ ጣሊያን ቤቱን ቢሰራውም ቦታው የመድሀኒ ዓለም ቤተክርስቲያን ለመሆኑ ብዙ መረጃወች አሉ።
በክፍል አንድ ላይ ለመጠቆም እንደሞከርነው ጣሊያን ሲገባ የከተማዋ ነዋሪ ወደ ገጠር የሸሸው ሸሸ ሌላው ደግሞ በረሀ በመግባት ለነፃነቱ ይዋጋ ነበር።
ለዚህም ነበር ከነፃነት በኋላ የመሬት ባለቤቶች የይገባኛል ክርክር የጀመሩት። ለምሳሌ ያህል ፒያሳ ሳንወጣ አሁን ያለው አይቀር ሆቴል ልክ ጣሊያን ሲወጣ ራስ ውብነህ ሆቴል ይባል ነበር። ባለቤቱም አርበኛው ራስ አሞራው ውብነህ ንጉሡ የሰጧቸው ነበር።
ይህ በዲህ እንዳል የመሬቱ ባለቤት ግን እሙሀይ አጀቡሽ ጉበና የተባሉ የትንሽቱ አራዳ ነዋሪ ለ30 ዓመታት የርስት የይገባኛል ክስ ላይ እንደነበሩ ድፍን ጎንደር ያውቃል።
እሙሀይ አጀቡሽ የደጃዝማች ካሣ መሸሻ አማት ነበሩ።
ሲኒማ ቤቱን ያደሱትና ሥራ ላይ እንዲውል ያደረጉት፣ በጣም በስራቸው የተመሰገኑት የጎንደር አገረ ገዥ ጀኔራል መርዕድ መንገሻ (see picture)ነበሩ።
ግማሹ የሲኒማ ቤቱ አዳሬሽና ቡናቤቱ የተገነባበት መሬት የተወሰነው የወይዘሮ ድንቅነሽ የተባሉ መሀን ሴት እንደነበሩ ገሚሱ ደግሞ አራጣ በማበደር የሚታወቁት የወይዘሮ ነጠረች ዕርስት እንደነበረና በኋላም ወይዘሮ ነጠረች ክርክሩን በማሸነፍ ከሲኒማቤቱ ጀርባ ኤክስፖ ሆቴል ብለው እንደገንቡ ይታወቃል።
የአፄ ፋሲል ቤተ መንግስት (see Picture) ስለመበላሸትና ራስ አሥራተ ካሣ የጎንደር አገረ ገዥ የገጠማቸውን ችግር ተለምዶዋዊውና ፍቅራዊው ሰላምታችን ይኸን የሽቦ ገመድ አልባ
ዘመናዊ መገናኛ አሳብሮና ሰንጥቆ በያላችጉሁበት ይድረስልን እንላለን።
….በሉ እንግዲህ ወደ ፒያሳ እንውጣ ሱቁን ከተማውን አስሰን እንድንመጣ ወደ ቀደመው ጉዳያችን እንመለስንና ክፍል ሁለትን የደመደምነው የፋሲል በተመንግስት የገጠመውን ችግር እናነሳለን ብለን ነበር የተለያየነው ይሁንና አንዱን እንደ ስሚዛ ስንመዝ ሌላው ተከተለና አሁንም ስለ ጎንደርና ጣሊያን ሰለሰሯቸው ህንፃወች ሌሎች አዳዲስ የታሪካዊ መረጃወች እናንተም የምትካፈሉበት ይዘን እዚያው ፒያሳ ጀምረን ወደ ጨዋ ሰፈር ካልመሸብን ብልኮ ደርሰን ወደ ኦቶባርኮ እንዋባለን።
የወራሪው የጣሊያን ፋሽስት መንግስት ጎንደርን ለምን መርጦ ከተመ የሚል ጥያቄ በኛም በእናንተም አዕምሮ አጭሯል ብለን እናምናለን። ብዙ መላምቶች ይኖሩ ይሆናል እኛ ያገኘነውን መረጃ እናቅምሳችሁ።
በኢትዮጵያ የቀደምት የነገስታት ታሪክ ማለትም ሰለሞናዊ ነገስታት ተብለው የሚጠሩት ሁላችንም እንደምናውቀው ከየኩኑ አምላክ እስከ አፄ ሱሲኒወስ ድረስ ቋሚ ነገስታቶች የቆረቆሩት ከተማ አልነበረም። በዘመናቸው የነገሡ ነገስታት አንዱ በጀመረው ከተማ የመቀጠልና የማስፋት ዝንባሌ አልነበረም ዳሩግን ዘላናዊ ንግስና እንደነበራቸው ነው የሚተረከው።
አፄ ፋሲለደስ (ፋሲል) አባታቸው አፄ ሱሲኒወስ የቆረቆሯትን ደንቀዝንና ቤተምንግስቱን ትተው ወደ ጎንደር እስኪመጡ ድረስ ማለትም በ1628 ዓመተ ምህረት በፈረንጆች 1636 ማለት ነው ጎንደር በጣም ትንሽ መንደርና ብዙ የሕዝብ ቁጥር አልነበራትም።
ይህን እውነታ አፄ ፋሲል አስረግጠው በማወቅና በመረዳት ከዚያም በተጨማሪ ጎንደር ዙሪያዋን በተራሮች ሰንሰለት የተከበበች ስለሆነች ከጠላት ለመመከት የሚስችል ቁልፍ ቦታ ናት ብለው እራሳቸውን በማሳመናቸው ሌላውና ዋና የወፋሲሳኔቸው ምንጭ ደግሞ ጎንደር ሁለት ታላላቅ ወንዞችን ማለትም አንገረብንና ቀኋን የተንተራሰች በመሆኗ ከሌሎች ቦታወች ሁሉ አንቺ የተባረክሽ ነሽ እና ንግስናየ ቤተ መንግስቴ እና ግዛቴን እስከ ዐለተ ሞቴ እዝችው ከአንቺ ጋር ይሁን በማለት አፄ ፋሲል የአባታቸው አፄ ሱሲኒወስን ቤተምንግስት ትተው ከደንቀዝ ሰሜናዊ ምዕራብ ወደ ምትገኘው ወደ ጎንደር ሰራዊታቸውን አስከትለው በመጓዝ ግዛታቸውን ያዛወሩት።
ጎንደር እንደገቡም ቤተ መንግስታቸው እስኪታነፅ በቀጥታ ያረፉት ከታሪካዊው ጃንተከል ዋርካ ሥር አጅባራቸውን ተክለው እንደነበር የታሪክ ድርሳናት ያሳያሉ።
በዚህ ጊዜም ነበር አውሮፓዊያን ወደ ጎንደር መምጣት የጀመሩት። ብዙ የታሪክ ተመራማሪወች እንደፃፉት መፃህፍት እንደፃፉት በታሪክም እንደምንሰማው ፒተር ሄይሊል የተሰኘ ጀርመናዊ ህግና ሥነ-ሃይማኖትን በፈረንሳይ ዋና መዲና በፓሪስ (ከ 1620 እስከ 1624) በመማር ትምህርቱን በማጠናቀቅ በርካታ ተመራማሪ ተማሪዎች ጋር በመሆን መጀመሪያ ወደ ግብፅ ቆይታ በማድረግላ እ.ኤ.አ በ 1629 ወደ ኢትዮጵያ በመጓዝ በሀገሪቱ ውስጥ ተፅዕኖ ፈጣሪ አገልጋይ, አስተማሪ እና ሐኪም በመሆን ንጉስ ፋሲለደስን አግልግሏል። በዚያን ጊዜ የነበሩ የቤተክህነት አባቶችንንና ቀሳውስትንም የግሪክና የይብራይስጥ ቋንቋን በማስተማር ይረዳ እንደነብር ታሪክ ያውሳል።
አፄ ፋሲልም በሚሰራቸው ስራወች በጣም በመደሰት ማሪያማዊት የተሰኘች ሴት ልጃቸውን
ለፒተር ለመዳር ውጥን ላይ እንደነበሩ የአዲስ ኪዳን መፅሐፍ ቅዱስን ወደ አማርኛ እዛብቶ ሲትርጉም ስላገኙት በአስቸኳይ ከሀገር እንዲወጣ ንጉስ ፋሲል በማዘዛቸው ከሀገር ተባረረ።
ከላይ ለማሳየት እንደሞከርነው አፄ ፋሲል ጎንደርን ለከተማነት ያጩበት ሁለት ውሳኒያዊ ነጥቦች ነበሩ። የፋሽስት ጣሊያን የጦር ኋይል ኢትዮጵያን ከወረረ በኋላ ጎንደር ከተማ ላይ ያተኮረበት ዋናው ምክንያቱ ሁለቱ ወንዞች ማለትም የአንገረብና የቀኋ እንደነበሩና ሌላው ደግሞ የጎንደር አካባቢው የሰባ መሬትን በመስኖ እየታገዘ መለስተኛ እርሻወችን ለመመስረት እቅድ እንደነበራቸው እኛ ፒያሳወች ቆፍረንና ፈልሰን ያገኘናቸው ታሪካዊ መረጃወች አረጋግጠውለናል።
በቅምሻ ቁጥር አንድ ጣሊያን ጎንደር ከተማ 352 ህንፃወችን መገንባቱን እናስታውሳለን። እነኝህ በመቶ የሚቆጠሩ ህንፃወች ከመገንባታቸው በፊት የከተማዋን ፕላን ያወጣው ገራርዶ በዕሲዮ Gherardo Bosio (ፎቶውን የመልከቱ) የተሰኘ ኢንጂነር ነበር። Gherardo በ1918 ዓመተ ምህረት ወይንም በፈረንጆች በ1926 በሮማን ኢንጂነሪንግ በዲግሪ የተመረቀ ሲሆን ከዚያም በ1923 ዓመተ ምህረት ወይንም በፈረንጆች በ1931 በፍሎራንስ ዩኒቨርሲቲ የህንፃ ትምህርት ቤት ተመርቆ ኢትዮጵያ ጎንደርና ደሴን ከዚያም ደግሞ የአልባኒያን ዋና ከተማ ቲሪና ማስተር ፕላን Masterplan of Tirana, Albania በ1939 በፈረንጅ ምስራቱን ታሪክ ያስተምረናል።
ገራርዶ የጎንደርን ማስተር ፕላን ሲሰራ የተሰጠው ትዕዛዝ የሚሰሩ ቤቶች ሁሉ አንገረብንና ጣና ሀይቅን እንዲያሳዪ ሆነው እንዲገነቡ ነበር የተሰጠው የስራ ሀላፊነት። በዚህም ምክንያት ጎንደር ጨዋ ሰፈር 2020 ጫማ ከባህር ወለል በላይ በመሆኗና አንገርብ ወንዝን በደንብ ስለምታሳይ ታቅዶ በጠቅላላው 35 ህንፃወች ሲገነቡ ከነዚህም ውስጥ ሰባት ቪላዎች እና 28 ህንጻዎች ተገንብተዋል።
ሌላው ጨዋ ሰፈር ውስጥ ሁለት ባንኮችን ባንካ ዲ-ኢታሊያና Banca d’Italia እና ባንኮ ዲ-ሮማ Banco di Roma. አንደኛው አሁንም በባንክነት እያገለገለ የሚገኘው ዋና ባንክ በመባል የሚታወቀው ሲሆን ሁለተኛው በአሁኑ ሰዓት ከግልጋሎት ውጭ ሲሆን ለረጅም ጊዜ በእስር ቤትነት 1ኛ ፖሊስ ጣቢያ የነበረው ነው።
ጨዋ ሰፈር ይኖሩ የነበሩ ጣሊያኖች በእረፍት ጊዚያቸውን የሚያሳልፉት አንገረብ በመዋኘት እንደነበርም ይነገራል ለዚያም ነበር አንገረብ ጥሊያን መዋኛ በመባል ይጠራ የነበረው።
አሊቤርጎ ቻው ወይንም (እቴጌ መነን///ተራራ ሆቴል) እዚህ ፕላኑ ላይ እንደሚታየው መዋኛ፣ ቡና ቤት፣ የመሬት ቴንስ እንዱም ብዛት ያላቸው መኝታ ቤቶችን ያካተተ ትልቅ ሆቴል ሲሆን የታለመለት ለፋሲል ቤተ መንግስት እንዲቀርብና አንገረብንና ጣናን እንዲያሳይ ሆኖ ነበር የተገነባው። የታሪክ መረጃወቻችን እንደገለፁት በግንባታው ረዥም ጎዜ ወስዶ ነበር።
አሊቤርጎ ቻው ግንባታ በነበረበት ወቅት ሁለቱ ትናንሽ ሊቶሮዮ እና ቺንጎ Littorio and Cigno የተሰኙ ሆቴሎች እያንዳንዳቸው 7 የመኝታ ክፍሎች የነበሯቸው እንደነበሩ ታሪክ ያወሳል። ሁለት ምግብ ቤቶች Fior del Tanaና Trattoria Romagnola የተባሉ ጣሊያኖችን ግልጋሎት ይሰጡ ነበር።
ቸር ይግጠመን
Gondar Piasssa
Filed in: Amharic
-
የጎንደር ከተማ በ1808
-
የጎንደር ከተማ በ1854
-
የጎንደር ከተማ በ1876
-
የጎንደር ከተማ በ1876
-
የጎንደር ከተማ በ1877
-
የጎንደር ከተማ በ1927
-
የጎንደር ግምብ አንድ አንድ ክፍሉ ሳይፈራርስ
ኢትዮጵያ |
ታሪካዊ ቦታዎች • አክሱም • ላሊበላ • ጎንደር • ነጋሽ • ሐረር • ደብረ-ዳሞ • አዲስ አበባ |
|