Jump to content

አዲስ አበባ

ከውክፔዲያ
(ከአዲስ ኣበባ የተዛወረ)


አዲስ ፡ አበባ
የአዲስ አበባ ሰማይ ጠቀሰ ህንፃዎች 2023
አገር  ኢትዮጵያ
የተቆረቆረችው ፲፰፻፸፰
ከንቲባ አዳነች አቤቤ (ምክትል)
የቦታ ስፋት
   • አጠቃላይ 527
ከፍታ 2,355 ሜ.
የሕዝብ ብዛት
   • አጠቃላይ 3,384,569
ድረ ገጽ addisababacity.gov.et
አዲስ ፡ አበባ is located in ኢትዮጵያ
{{{alt}}}
አዲስ ፡ አበባ
የአዲስ ፡ አበባ ፡ አቀማመጥ ፡ በኢትዮጵያ ፡ ውስጥ

9°2′ ሰሜን ኬክሮስ እና 38°42′ ምሥራቅ ኬንትሮስ

አዲስ አበባ (Addis Abeba) ፤ የኢትዮጵያ ዋና ከተማ ስትሆን በተጨማሪ የአፍሪካ ሕብረት መቀመጫ እንዲሁም የብዙ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ቅርንጫፎችና ሌሎችም የዓለም የዲፕሎማቲክ (የሰላማዊ ግንኙነት) ልዑካን መሰብሰቢያ ከተማ ናት ። ራስ-ገዝ አስተዳደር ስላላት በኢ.ፌ.ዲ.ሪ ህገመንግስት የፌደራል ከተማነትን ማዕረግ ይዛ ትገኛለች። ከባሕር ጠለል በ2500 ሜትር ከፍታ ላይ የምትገኘው ከተማ በ1999 አ.ም በተደረገው የህዝብ ቆጠራ ወደ 2,739,551 በላይ ሕዝብ የሚኖርባት በመሆኗ የሀገሪቱ ትልቋ ከተማ ናት።[1]

ከተማዋ እቴጌ ጣይቱ በመረጡት ቦታ ማለትም በፍልውሐ አካባቢ ላይ በባላቸው በዳግማዊ ምኒልክ፲፰፻፸፰ (1878) ዓ.ም. ተቆረቆረች። የሕዝቧ ብዛት በያመቱ 8% (ስምንት በመቶ) እየጨመረ አሁን ወደ አምስት ሚሊዮን እንደሚደርስ ይገመታል።

እንጦጦ ጋራ ግርጌ ያለችው መዲና የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መገኛ ነች። ይህም በመስራቹ የቀድሞው ንጉሠ-ነገሥት ስም ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ ይባል ነበር።

በዓለም ዙሪያ ካሉ ወደ 1,000 የሚጠጉ ሰዎች በዘረመል መረጃ ላይ የተመሰረተ ጥናት የሰው ዘር ከአዲስ አበባ ቅርብ ከሆነ ቦታ ከ100,000 ዓመታት በፊት እንደተበተነ ያመለክታል።[2]

መካከለኛው ዘመን

[ለማስተካከል | ኮድ አርም]

የመካከለኛው ዘመን ነገሥታት መዲና የነበረው በራራ ተብሎ ለሚጠራው ቦታ ከቀረቡት ጥቂት ቦታዎች መካከል ከአሁኑ አዲስ አበባ በስተሰሜን የሚገኘው እንጦጦ ተራራ ላይ ያለ ከፍ ያለ ጠፍጣፋ መሬት ነው። ይህ ቦታ እስከ 16ኛው መቶ ክፍለ ዘመን የዐጼ ልብነ ድንግል አገዛዝ ድረስ የበርካታ ነገስታት ዋና መኖሪያ ሆኖ አገልግሏል።[3]

በ1442 ዓ.ም አካባቢ ጣሊያናዊው የካርታ ባለሙያ ፍራ ማውሮ ባሳለው ካርታ ላይ ከተማዋን በዝቋላ ተራራ እና በመንጋሻ መካከል አስቀምጧታል። ሆኖም ግን የመናዊው ጸሃፊ አረብ-ፋቂህ እንደዘገበው በ1521 ዓ.ም የንጉሠ ነገሥቱ ጦር ከአዋሽ ወንዝ በስተደቡብ ተይዞ ሳለ በግራኝ አህመድ ተመትታለች። በራራ የሚገኘው በእንጦጦ ተራራ ላይ ነው የሚለው ሀሳብ የሚደግፈው በ19ኛው መቶ ክፍለ ዘመን መገባደጃ ላይ የተመሰረተውና በዓለት በተፈለፈለው ዋሻ ሚካኤል እና በእንጦጦ ማርያም ቤተ ክርስቲያን መካከል የሚገኝ ትልቅ የመካከለኛው ዘመን ከተማ በመገኘቱ ነው። በ30 ሄክታር ቦታ ለ ያረፈው ይህ ጥንታዊ ከተማ ከ 520 ሜትር የድንጋይ ግንብ እስከ 5 ሜትር ቁመት ያላቸው 12 ማማዎች ያሉት ቤተመንግስት ያካትታል።[3]

ከከተማዋ በፊት የኢትዮጵያ ዋና ከተማ የነበረችው እንጦጦ የተመሰረተችው በዳግማዊ ዐጼ ምኒልክ በ1871 ዓ.ም ነበር። በወቅቱ የሸዋ ጠቅላይ ግዛት ንጉስ የነበሩት ምኒልክ የእንጦጦ ተራራን በደቡብ ወታደራዊ ዘመቻቸው ጠቃሚ መሰረት አድርገው አገኙት። በስፍራው የነበረውንም ፍርስራሽ እና ያልተጠናቀቀ የመካከለኛው ዘመን ውቅር ቤተክርስቲያን ጎበኙ። ሚስታቸው እቴጌ ጣይቱ ቤተክርስቲያን በእንጦጦ ላይ መስራት በጀመሩበት ወቅት፣ የምኒሊክ ዝንባሌ ወደእዚህ ስፍራ በተለይ ተሳበ፤ ሁለተኛም ቤተክርስቲያን ባቅራቢያው ሠሩ። ነገር ግን ማገዶም ሆነ ውኃ በማጣት ምክንያት አካባቢው መንደር ለመመሥረት አይመችም ነበር፤ ስለዚህ ሰፈራው የጀመረበት ከተራራው ትንሽ ወደ ደቡብ በሚገኘው ሸለቆ ውስጥ በ1878 ነበረ። [4]

የጼ ምኒሊክ ቤተመንግስት በርቀት 1892 አ.ም

እቴጌ ጣይቱ እርሳቸውና የሸዋ ቤተመንግስት ወገን መታጠብ ይወዱ የነበረበት ፍልወሃ ምንጭ አጠገብ ለራሳቸው ቤት ሠሩ። አዲስ አበባ (ወይም ባጭሩ «አዲስ») ተብላ የተሠየመችው እቴጌ ጣይቱ ኅዳር ፲፬ ቀን ፲፰፻፸፱ (1879) ዓ.ም. ፍልወሃ ምንጭ ወርደው ሳሉ ከዚህ በፊት አይተዋት የማያውቋት አንዲት ልዩ አበባ አይተ ስለማረከቻቸው ቦታውን ‹‹አዲስ አበባ!›› አሉ ይባላል። ከእዚያ በኋላ ሌሎች መኳንንቶች ከነቤተሰቦቻቸው አቅራቢያውን ሠፈሩ፤ ምኒልክም የሚስታቸውን ቤት ቤተመንግሥት እንዲሆን አስፋፉትና እስከ ዛሬ ድረስ ቤተ መንግሥት ሆኖ ቆይቷል። ምኒልክ የኢትዮጵያ ንጉሰ ነገሥት በሆነበት ወቅት በ1881 ዓ.ም አዲስ አበባ የኢትዮጵያ ዋና ከተማ ሆነች። ከእዚያ ጀምሮ ከተማዋ ለመኳንንቶች ብቻ ሳይሆን የእጅ ጥበብ ባለሙያዎችን፣ ነጋዴዎችን እና የውጭ ሀገር ጎብኝዎችን ጨምሮ በርካታ የስራ ክፍሎችን በመሳብ አደገች።

ቀደምት የመኖሪያ ቤቶች ጎጆዎች ነበሩ። የአዲስ አበባ ዕድገት የጀመረው ያለቅድመ ዕቅድ በተከሰተ ፈጣን የከተማ መስፋፋት ነው። ከአፄ ምኒልክ አስተዋፅዖዎች አንዱ ዛሬም በከተማው ጎዳናዎች የሚታዩት በርካታ የባሕር ዛፎች ተከላ ነው። እንደ ሪቻርድ ፓንክረስት ገለጻ የከተማዋ የተፋጠነ የህዝብ ቁጥር መጨመር ምክንያት በጊዜያዊ ገዥዎች እና በወታደሮቻቸው፣ በ1892 ረሃብ እና የአድዋ ጦርነት ምክንያት ነው። ሌላው የ1899 የመሬት ህግ፣ በ1901 የማዘጋጃ ቤት አስተዳደር እና ከ20ኛው ክፍለ ዘመን ጀምሮ የነበረው የባቡር እና የዘመናዊ የትራንስፖርት ስርዓት እድገት ነው።

20ኛው ክፍለ ዘመን

[ለማስተካከል | ኮድ አርም]

ቅድመ-ጣሊያን ወረራ (1908-1927)

[ለማስተካከል | ኮድ አርም]
አዲስ አበባ ((እንግሊዝኛ) ቪድዮ)፣ 1927 ዓ.ም. ከጣሊያን ወረራ በፊት

በ1908 አቶ ገብረህይወት ባይከዳኝ የዋና ዋና የአስተዳደር ክፍሎችና የኢትዮ– ጅቡቲ የባቡር መስመር አስተዳዳሪ ሆኑ። በ1909 ራስ ተፈሪ መኮንን፣ (በኋላም ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ) ከተሾሙ በኋላ በከተማዋ ከፍተኛ ሰው ነበሩ። ከዚህ ጊዜ ጀምሮ ራስ ተፈሪ በ1910 እንደ እንደራሴ ህጋዊ ስልጣን አግኝተዋል። የዘመናዊነትንና ከተሜነትን አስፈላጊነት በመገንዘብም ከተማዋን ወደ ለውጥ ለማምጣት ጥረት ያበረከቱ ሲሆን ሀብት ክፍፍልም አድርገዋል። በ1918 እና 1919 መጠነ ሰፊ የኢኮኖሚ አብዮት ተፈጠረ ፣ በካፒታል ክምችት ምክንያት የተትረፈረፈ የቡና ምርት ማደግ ጀመረ ።መካከለኛው የህብረተሰብ ክፍል ከዚህ ሃብት በማትረፍ ከውጪ የሚገቡ የአውሮፓ የቤት እቃዎች እና አዳዲስ አውቶሞቢሎችን በማስመጣት፤ ባንኮችን በማስፋፋትና አዳዲስና በድንጋይ የተገነቡ ቤቶችን በመስራት ከተማዋን ተጠቃሚ አድርገዋል። በ1918 የተሽከርካሪዎች አጠቃላይ መዝገብ 76 ሲሆን በ1922 ወደ 578 ደርሷል። የመጀመሪያው የመንገድ ትራንስፖርት በአዲስ አበባ እና በጅቡቲ መካከል በደሴ አቅጣጫ የተከፈተው አውራ ጎዳና ነው። አውራ ጎዳናው ለጅቡቲው የፈረንሳይ የባቡር መስመር ጠቃሚ ነበር። በ 1922 ንጉሠ ነገሥቱ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዘውድ ጭነው አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን እና የመሰረተ ልማት ግንባታዎችን ቀጥለዋል ። ከእነዚህም መካከል የኤሌክትሪክ መስመሮችንና ስልክ እንዲሁም እንደ ሚያዚያ 27 አደባባይ ያሉ በርካታ ሐውልቶችን ይካተታሉ።

በጣሊያን ወረራ ጊዜ (1928-1933)

[ለማስተካከል | ኮድ አርም]

1928 ዓ.ም. በጦርነት ጊዜ የፋሺስቶች ሠራዊት ከተማዋን ወርረው ዋና ከተማቸው አደረጉዋት፤ እስከ 1931 ድረስ የኢጣልያ ምስራቅ አፍሪቃ አገረ ገዥ ነበረባት።ከተማዋ ከወረራ በኋላ እስከ 1933 ድረስ የጣሊያን ምስራቅ አፍሪካ ዋና ከተማ ሆና ነበረች። በ1933 ከተማይቱ በሜጀር ጄነራል ዊንጌት እና በአፄ ኃይለ ሥላሴ የኢትዮጵያ ጌዲዮን ሃይል እና የኢትዮጵያ ንቅናቄ ነፃ ወጣች። አፄ ኃይለ ሥላሴም ከሄዱ ከአምስት ዓመታት በኋላ ግንቦት 5 ቀን 1941 ዓ.ም. ተመለሱ።

የድህረ-ጣሊያን ወረራ (1933-1966)

[ለማስተካከል | ኮድ አርም]
ፒያሳ አካባቢ ያለው ጣይቱ ሆቴል

በ1938 አጼ ኃይለ ሥላሴ ከተማዋን የአፍሪካ ዋና ከተማ እንድትሆን ንድፍና እና የማስዋብ ግቦችን ለማሰራት ታዋቂውን እንግሊዛዊ ማስተር ፕላን ሰሪ ፓትሪክ አበርክሮምቢን ጋበዙ። ማስተር ፕላኑ በ1935 ከነበረው የለንደን የትራፊክ ችግር ተሞክሮ በመውሰድ የዋና ዋና የትራፊክ መስመርና የሰፈር ክፍሎችን ጥንቃቄ በተሞላበት መልኩ በመለየት ተጠናቀቀ።[5]

ኃይለ ሥላሴ በ1963 በኋላም በ1994 ፈርሶ በአፍሪካ ኅብረት የተተካውን የአፍሪካ አንድነት ድርጅት እንዲመሰርትም ረድተው ነበር፣ ዋና መሥሪያ ቤቱም በከተማዋ ነው። የተባበሩት መንግሥታት ምጣኔ ሀብት ጉባኤ ለአፍሪቃ ደግሞ ጠቅላይ መሥሪያ ቤት ባዲስ አበባ አለው። በ1957 ዓ.ም. አዲስ አበባ ለኦርቶዶክስ አብያተ ክርስቲያናት ስብሰባ ሥፍራው ነበረች።

እ.ኤ.አ. በ1957 የተማሪዎች ሰልፍ “መሬት ላራሹ” በሚል መፈክር በማሰማት በኢትዮጵያ የማርክሲስት ሌኒኒስት እንቅስቃሴ ተካሂዷል። በተጨማሪም በ1955 የተከሰተው የነዳጅ ቀውስ በከተማይቱ ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ አሳድሯል። በ1966 ዓ.ም ሃይለስላሴ ከስልጣናቸው በፖሊስ አባላት ወረዱ። በኋላም ቡድኑ በይፋ “ጊዜያዊ ወታደራዊ አስተዳደር ምክር ቤት” በማለት ራሱን ደርግ ብሎ ሰየመ። በወቅቱ ከተማዋ 10 ወረዳዎች ብቻ ነበሩት።

የደርግ አስተዳደር (1966-1983)

[ለማስተካከል | ኮድ አርም]

ደርግ ስልጣን ከያዘ በኋላ በግምት ሁለት ሶስተኛው ቤቶች ወደ ኪራይ ቤት ተዛወሩ። የህዝብ ቁጥር ዕድገት ከ6.5% ወደ 3.7% ቀነሰ። በ1975 ደርግ በግል ባለ አክሲዮኖች የተገነቡ “ተጨማሪ” የኪራይ ቤቶችን የአገር ንብረት አደረገ። በመሆኑም በአዋጅ ቁጥር 47/1975 የተዳከሙ ቤቶች(ከጭቃ የተገነቡ) በቀበሌ ቤቶች ይተዳደራሉ፣ ጥራት ያላቸው የኪራይ ቤቶች ደግሞ በኪራይ ቤቶች አስተዳደር ኤጀንሲ (ARHA) ስር ይሆናሉ። እነዚያ የኪራይ ቤቶች ዋጋ ከ100 ብር (48.31 የአሜሪካ ዶላር) በታች ከሆነ በቀበሌ አስተዳደር ሥር ይሆናል። ይህን ተከትሎ የአስተዳደር ክፍፍሉ ወረዳዎች ወደ 25 እና 284 ቀበሌዎች አድጓል።[6]

በደርግ ጊዜ የሃንጋሪው አርክቴክት ፖሎኒ በከተማ ልማትና ቤቶች ሚኒስቴር እገዛ የከተማውን ማስተር ፕላን የጀመረው የመጀመሪያው ሰው ነው ፖሎኒ በጊዜው አብዮት አደባባይ ተብሎ የተጠራውን የመስቀል አደባባይን በአዲስ መልክ በመንደፍ ሠርቷል።

ኢ.ፌ.ዲ.ሪ (1983-አሁን)

[ለማስተካከል | ኮድ አርም]
T-55 ታንክ በአዲስ አበባ ጎዳናዎች ላይ። ግንቦት ፤ 1983

ደርግን ለመጣል እየታገለ የነበረው ጥምር ፓርቲ የኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ዲሞክራሲያዊ ግንባር (ኢህአዴግ) ግንቦት 20 ቀን 1983 አዲስ አበባን ተቆጣጠረ። ተዋጊዎች 4ኪሎ ቤተመንግስት ታንክና ከባድ መሳርያ ታጥቀው ገቡ። ከአንድ ዓመት በኋላ አዲሱ የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ሕገ መንግሥት ወጣ። ሁሉም የኢትዮጵያ ከተሞች ተጠሪነታቸው ለክልል አስተዳደር ሲሆን፣ አዲስ አበባ (አዋጅ ቁጥር 87/1997) እና ድሬዳዋ (አዋጅ ቁጥር 416/2004) እራስን በራስ የማስተዳደር እና የልማታዊ ማዕከልነት ስልጣን ያላቸው ቻርተርድ ከተሞች ሆኑ።

በሚያዝያ 25/2007 ዓ.ም የአዲስ አበባን ድንበሮች በ1.1 ሚሊዮን ሄክታር ወደ ኦሮሚያ ልዩ ዞን ለማስፋፋት የተዘጋጀው አወዛጋቢ ማስተር ፕላን፣ የ2007ቱን የኦሮሞ ተቃውሞ አስነስቷል። መንግስት በሰላማዊ ሰልፈኞች ላይ በመተኮስና በድብደባ የሰጠው ምላሽ ወደ ለየለት አድማና ተቃውሞ አባባሰው። አወዛጋቢው ማስተር ፕላን በጥር 12 ቀን 2008 ተሰርዟል።በዚያን ጊዜ 140 ተቃዋሚዎች ተገድለዋል።

በአብይ አህመድ የጠቅላይ ሚኒስትርነት ጊዜ በአዲስ አበባ እና አካባቢዋ "ሸገርን ማስዋብ" የተሰኘ ስራ ተካሂዷል። ይህ ፕሮጀክት የከተማዋን አረንጓዴ ሽፋንና ውበት ለማሳደግ ያለመ ነው። 2010 ዶ/ር አብይ ከእንጦጦ ተራሮች እስከ አቃቂ ወንዝ ድረስ 56 ኪሎ ሜትር የወንዝ ዳርቻዎችን ለማስፋፋት ያቀደውን "የአዲስ አበባ ወንዞች ዳርቻዎች ልማት ፕሮጀክት" የተሰኘ ፕሮጀክት አስጀመሩ።

የአዲስ አበባ ከተማ ሠፈሮች ስያሜያቸውን ያገኙት በተለያዩ ምክንያቶችና አጋጣሚዎች ነው። እነዚህንም በተለያዩ ዘርፎች ከፍሎ በቅደም ተከተል ማየት ይቻላል።[7]

በርካታዎቹ የከተማዋ ቀደምት ሠፈሮች ስያሜያቸውን ያገኙት በቤተ-መንግሥቱ ዙሪያ መሬት በጉልት መልክ በተሠጣቸው መሣፍንቶችና መኳንንቶች ስም ነው። በዚህ መልክ ስያሜያቸውን ካገኙት ሠፈሮች መካከል ራስ መኮንን ሠፈር፣ ራስ ተሰማ ሠፈር፣ ራስ ብሩ ሠፈር፣ ፊታውራሪ ሀብተ ጊዮርጊስ ሠፈር፣ ራስ ስዩም ሠፈር፣ ደጃዝማች ውቤ ሠፈር፣ ነጋድራስ ኃይለ ጊዮርጊስ ሠፈር ፣ ደጃዝማች ዘውዱ አባኮራን ሠፈር እና ሸጎሌ (የአሶሣ ገዢ በነበሩት በሼክ ሆጀሌ አል ሐሠን የተሠየመው) ሠፈር ይጠቀሳሉ።[7]

ከእነዚህ ሠፈሮች መካከል ደጃዝማች ውቤ ሠፈር በተለይ ከጣሊያን ወረራ በፊት በሴተኛ አዳሪነት የሚተዳደሩ ነዋሪዎች በከፍተኛ ደረጃ ከሚገኙባቸው የከተማዋ ሠፈሮች አንዱ እንደነበረ ይነገራል። በዚህም ሳቢያ በስነ ቃል በርካታ ግጥሞች በዚህ ሠፈር ዙሪያ ተገጥመዋል። ከነዚህም መካከል፣

«ደጃች ውቤ ሠፈር ምን ሠፈር ሆነች፣
ያችም ልጅ አገባች ያችም ልጅ ታጨች።
ደጃች ውቤ ሠፈር ሲጣሉ እወዳለሁ፣
ገላጋይ መስዬ እገሊትን አያለሁ።

ደጃች ውቤ ሠፈር የሚሠራው ሥራ፣
ጠይሟን በጥፊ ቀይዋን በከዘራ»

የሚሉት ይገኙበታል።[7] በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ ከመላው የአገሪቱ ማዕዘናት መጥተው አዲስ አበባ በሠፈሩ ብሔረሰቦች የተመሠረቱ ሠፈሮች ይጠቀሳሉ። በዚህ መልክ ከተመሠረቱት ሠፈሮች መካከል ለአብነት አደሬ ሠፈርጎፋ ሠፈርወሎ ሠፈርወርጂ ሠፈርመንዜ ሠፈርሱማሌ ተራ ይገኙበታል። የወርጂ ሠፈርን የመሠረቱት የወርጂ ብሔረሰብ አባላት በቆዳና በበርኖስ ንግድ የተሠማሩ እንደነበሩ ይነገርላቸዋል። በተመሣሣይ መልኩ የሱማሌ ተራ ነዋሪዎች ዋነኛ መተዳደሪያ የሻይ ቤት ሥራ እንደነበር ይታመናል።[7]

በሶስተኛ ደረጃ በተለያዩ ሙያዎች ተሠማርተው በተለይም በቤተ መንግሥቱ የተለያዩ የሥራ ድርሻዎች በነበራቸው ባለሙያዎች የተቆረቆሩ ሠፈሮችን እናገኛለን። እነዚህም ከብዙ በጥቂቱ ሠራተኛ ሠፈር፣ ዘበኛ ሠፈር፣ ሥጋ ቤት ሠፈር፣ ኩባንያ ሠፈር፣ ጠመንጃ ያዥ ሠፈር፣ ካህን ሠፈር (በኋላ ገዳም ሠፈር) ፣ ገባር ሠፈር ፣ ሠረገላ ሳቢ ሠፈርና ውሃ ስንቁ ሠፈርን ያካትታሉ። ሠራተኛ ሠፈር በአፄ ምኒልክ ቤተ-መንግሥት በዕደ ጥበባት ሙያ በተሠማሩ ነዋሪዎች የተመሠረተ ሠፈር ነው። የሠፈሩ መሥራቾች ዋነኛ ሙያ የብረታ ብረት ሥራ እንደነበረ ይነገራል። ይሄም የተለያዩ የብረታ ብረት ውጤቶችን ለምሣሌ ማረሻ፣ የፈረስ እርካብን፣ የቤት እቃዎችን፣ የጋሻና ጦር እና የጠመንጃ ዕድሳትን ይጨምራል። በቤተ መንግሥቱ በአናጢነት የተሠማሩ ባለሙያዎችም የሚኖሩት በሠራተኛ ሠፈር እንደነበር ይነገራል።[7]

በከተማዋ ከሚኖሩት የውጭ ተወላጆችም መካከል ጥቂቶቹ የሚኖሩት በዚሁ ሠፈር ነበር። ከነዚህም የውጭ ነዋሪዎች መካከል በግንባር ቀደምትነት የሚጠቀሱት አርመናዊው የግብረ ህንፃ ባለሙያ ሙሴ ሚናስ ሔርቤጊን ነበሩ። ዘበኛ ሠፈር የቤተ-መንግሥቱ ጠባቂዎች ወይም የዕልፍኝ ዘበኞች የሠፈሩበት ሠፈር ሲሆን፣ ገባር ሠፈር ደግሞ ከተለያዩ የአገሪቱ ክፍላተ ሀገር እንደ ማር፣ እህልና ከብት በመሣሠሉት ምርቶች ዓመታዊ ግብር ለመክፈል ወደ ከተማዋ በሚመጡ ግለሰቦች የተመሠረተ ሠፈር እንደሆነ ይነገራል። የውሃ ስንቁ ሠፈር መስራቾች ደግሞ መደበኛ ክፍያ የሌላቸው እና ስንቃቸው ውሃ ብቻ የሆነ የጦሩ አባላት የሠፈሩበት ሠፈር እንደነበረ ይነገራል።[7]

በሌላ በኩል ጥቂት የማይባሉ የአዲስ አበባ ሠፈሮች ስያሜያቸውን ያገኙት በተለያዩ አጋጣሚዎች፣ ክስተቶችና ታሪካዊ ክንዋኔዎች ነው። ሠባራ ባቡር ፣ እሪ በከንቱ ፣ ዶሮ ማነቂያ ፣ አፍንጮ በር ፣አራት ኪሎ ፣ ስድስት ኪሎ ፣ አምስት ኪሎ ፣ ጣሊያን ሠፈር፣ ሃያ ሁለት ማዞሪያ፣ ሽሮ ሜዳ እና ነፋስ ስልክ ተብለው የሚጠሩትን ሠፈሮች በዚሁ ዘርፍ መፈረጅ ይቻላል። ሰባራ ባቡር ሠፈር ስያሜውን ያገኘው ሙሴ ሰርኪስ ተርዚያን በሚባሉ አርመናዊ ነጋዴ አማካኝነት ከውጭ አገር መጥቶ አሁን ስያሜውን ባገኘበት ቦታ ተበላሽቶ በቀረው የመንገድ መሥሪያ ተሽከርካሪ (ሮለር) ምክንያት ሠፈሩ ሰባራ ባቡር እንደተባለ ይነገራል። አገሬው “የሠርኪስ ባቡር” እያለ የሚጠራው መሣሪያ አዲስ አበባ በደረሰ ጊዜ የሚከተለው ግጥም ተገጥሞለት ነበር።[7]

«ባቡሩ ሰገረ ስልኩም ተናገረ፣
ምኒልክ መልአክ ነው ልቤ ጠረጠረ።»[7]

በሌላ በኩል ከዐድዋ ጦርነት በኋላ በድል አድራጊው የኢትዮጵያ ሠራዊት የጦር ምርኮኞች የሆኑት የጣሊያን ተወላጆች በማረፊያነት የተመረጠው ቦታ ጣሊያን ሠፈር የሚለውን ስያሜ ማግኘቱ ይታወቃል። እንደዚሁም የስድስት ኪሎ ሠፈር ፣ አራት መንገዶች መገናኛ የሆነው አካባቢ አራት ኪሎ ሠፈር በሁለቱ ሠፈሮች መካከል ያለው አካባቢ ቆይቶ አምስት ኪሎ ሠፈር የሚለውን ስያሜ ማግኘቱም የሚታወቅ ነው።[7]

መድኃኔዓለም ካቴድራል አዲስ አበባ

ሌላው በከተማው ከሚገኙ ዋና ዋና ሠፈሮች መካከል በከተማዋ ቀደምት ነዋሪዎች በሆኑት የኦሮሞ ተወላጆችና የቦታ ስሞች የተሰየሙ ሠፈሮችን እናገኛለን። ከነዚህም መካከል ጉለሌ ፣ ጎርዶሜ ፣ ቀበና ፣ ኮተቤ ፣የካ ፣ እንዲሁም ገርጂ እና ላፍቶ የተባሉት ሠፈሮች ለአብነት ይጠቀሳሉ። ከእነዚህም ሠፈሮች መካከል በቀበና ወንዝ ስም በተሰየመው ቀበና ሠፈር ከተገጠሙት ግጥሞች አንዱን እንመልከት።

«ቀበና ለዋለ አራዳ ብርቁ ነው፣

አራዳም ለዋለ ቀበና ብርቁ ነው፣
እሱስ ላገናኘው ሴት ወይዘሮም ደግ ነው።»[7]

በሌላ ዘርፍ ከ1928 የጣሊያን ወረራ እና የአምስት ዓመት ቆይታ ጊዜ አንዳንድ የአዲስ አበባ ቦታዎች እና ሠፈሮች የጣሊያንኛ ስያሜ አግኝተዋል። ከእነዚህም መካከል መርካቶ (የአገሬው ገበያ) ፣ ፒያሣ (የቀድሞው አራዳ) ፣ ካዛንቺስ፣ ካዛ ፖፖላሬ እና ካምቦሎጆ ዋና ዋናዎቹ ናቸው። ካዛንቺስ ስያሜውን ያገኘው አዲስ አበባ በጣሊያን ይዞታ ስር በነበረችበት ጊዜ ለከፍተኛ የጣሊያን ሹማምንት መኖሪያ ቤቶች በሠራው የጣሊያን ኩባንያ ምህፃረ ቃል ሲሆን ካዛ ፖፖላሬ ደግሞ በዝቅተኛ ደረጃ ለሚገኙ ጣሊያናዊያን ቤቶች በሠራው በካዛ ፖፖላሬ ኩባንያ ስም ነው ስያሜውን ያገኘው። በሌላ በኩል ካምቦሎጆ ሠፈር መጠሪያውን ያገኘው ካምፖ አሎጅዬ ኦፔራ (Campo Allogio Opera) ከሚለው ስም ሲሆን ይሄም ማለት የሠራተኞች ካምፕ ማለት ነው።[7]

አዲስ አበባ መሃል ከተማ ከሰገር ፓርክ ታየ

እንዲሁም በከተማዋ በሚገኙ አብያተ ክርስቲያን እና አጥቢያዎች የተሰየሙ ሠፈሮች ሌላው ዋነኛ ዘርፍ ነው። በዚህ ዘርፍ ከሚገኙ ሠፈሮች መካከል ተቀዳሚውን ሥፍራ የሚይዘው አራዳ ጊዮርጊስ ሠፈር ነው። አራዳ በተለይም ከጣሊያን ወረራ ቀደም ባለው ጊዜ የአዲስ አበባ የኢኮኖሚ ማዕከል ከመሆኑ አኳያና በርካታ ማሕበራዊ ክንዋኔዎችን ያስተናግድ የነበረ ሠፈር እንደመሆኑ በስነቃል ብዙ ተብሎለታል። ለአብነት

«ሱሪ ያለቀበት አይገዛም አዲስ፣
ወይ አዲስ አበባ ወይ አራዳ ጊዮርጊስ።
እስኪ አራዳ ልውጣ ብርቱካን ባገኝ፣
ትናንት ኮሶ ጠጣሁ ዛሬ መረረኝ።
ምነው በአደረገኝ ከአራዳ ልጅ መሣ፣
እንኳን ለገንዘቡ ለነፍሱ የማይሣሣ።

የአራዳ ዘበኛ ክብሬ ነው ሞገሴ፣
በቸገረኝ ጊዜ የሚደርስ ለነፍሴ» የሚሉት ይገኙባቸዋል።[7]

በዚህ ዘርፍ የሚመደቡ ሌሎች ሠፈሮች ደግሞ አማኑኤል ፣ ዮሴፍ ፣ ኪዳነ ምሕረት ፣ ቀራኒዮ መድኃኔ ዓለም ፣ እና ቀጨኔ መድኃኔ ዓለምን ያካትታሉ። እ.ኤ.አ. ከ 1888 ዓ.ም. የዐድዋ ጦርነት ድል እና ከአዲስ አበባው ስምምነት በኋላ ጣሊያን፣ ሌሎች የአውሮፓ መንግሥታት እና አሜሪካ የአገራችንን ሉዓላዊነት በመቀበል ከኢትዮጵያ ጋር ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት መሥርተዋል። በዚህ ሂደት በርካታ አገሮች የነዚህን አገሮች ፈለግ በመከተል ኤምባሲዎቻቸውን በአዲስ አበባ ከፍተዋል። ከአዲስ አበባ በርካታ ሠፈሮች መካከል አንዳንዶቹ ስያሜያቸውን ያገኙት ከእነዚህ ኤምባሲዎችና ቀደም ሲል ደግሞ ከሌጋሲዮኖች ነው። ፈረንሣይ ሌጋሲዮንና ሩዋንዳ ሠፈሮች ለዚህ ጥሩ ምሳሌ ናቸው። በመጨረሻም ከአዲስ አበባ ሠፈሮች መካከል አንዳንዶቹ በታዋቂ የውጭ አገር ዜጎች ስም የተሠየሙ ናቸው። ከእነዚህም መካከል ቤኒን ሠፈር እና ተረት ሠፈር ይገኙበታል። ቤኒን ሠፈር ስያሜውን ያገኘው ከጣሊያን ወረራ በፊት ተዋቂ ነጋዴ በሆኑት የአይሁድ ተወላጅ ቤኑን ሲሆን ተረት ሠፈር ደግሞ ስያሜውን ያገኘው በአዲስ አበባ ከተከፈቱት ከመጀመሪያዎቹ ሆቴሎች አንዱ በነበረው በሆቴል ዳፍራንስ ባለቤት በሆኑት ፈረንሣዊው ሙሤ ቴረስ ስም ነው።[7] ተረት ሰፈር በጣም ታዋቂ የሆኑ አረብ እመቤት ይኖሩ ነበር ።የሰፈሩ ሰው እኚህን እመቤት <የተረት ሰፈር አድባር> ብሎ ይጠራቸው ነበር : ትክክለኛ ስማቸው ግን ወ/ሮ መርየም ቃሲም ሲሆን የሰፈሩ ሰው ያወጣላቸው የሁልግዜም መጠሪያ ስማቸው ግን "እሜት ማሪያም" ነበር ።የተረት ሰፈር ሰው ሆኖ እሜት ማሪያምን እና የመካሻ ማሞ ጋራጅን የማያውቅ የለም ።

ክፍለ ከተሞች

[ለማስተካከል | ኮድ አርም]

አዲስ አበባ በዐሥር ክፍለ ከተሞች እና በዘጠና ዘጠኝ ቀበሌዎች ትከፈላለች። ዐሥሩ ክፍለ ከተሞች ከዚህ በመቀጠል የተዘረዘሩት ናቸው።

ክፍለ ከተማ ስፋት (ካሬ ኪ.ሜ) የሕዝብ ብዛት ጥግግት ካርታ
1 አዲስ ከተማ[8] 7.41 271,664 36,659.1
2 አቃቂ ቃሊቲ[9] 118.08 195,273 1,653.7
3 አራዳ[10] 9.91 225,999 23,000
4 ቦሌ[11] 122.08 328,900 2,694.1
5 ጉለሌ[12] 30.18 284,865 9,438.9
6 ቂርቆስ[13] 14.62 235,441 16,104
7 ኮልፌ ቀራንዮ[14] 61.25 546,219 7,448.5
8 ልደታ[15] 9.18 214,769 23,000
9 ንፋስ ስልክ ላፍቶ[16] 68.30 335,740 4,915.7
10 የካ[17] 85.46 337,575 3950.1

ለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ በ2012 አስራ አንደኛው የአዲስ አበባ ክፍለ ከተማ ሆኖ ተጨምሯል።

የስነ ሕዝብ አወቃቀር

[ለማስተካከል | ኮድ አርም]

በ1999 የኢትዮጵያ ብሄራዊ ስታስቲክስ ባለስልጣናት ባደረገው የህዝብ ቆጠራ አዲስ አበባ በአጠቃላይ 2,739,551 የከተማ እና የገጠር ነዋሪዎች አሏት። ለዋና ከተማው 662,728 አባወራዎች በ628,984 መኖሪያ ቤቶች ውስጥ እንደሚኖሩ ተቆጥሯል, ይህም በአማካይ 5.3 ሰዎች በአንድ ቤተሰብ ማለት ነው።. ሁሉም የኢትዮጵያ ብሔረሰቦች በአዲስ አበባ የሀገሪቱ ዋና ከተማ በመሆኗ የተወከሉ ቢሆንም፣ ትልቁ የአማራ (47.05%)፣ ተከትሎም ኦሮሞ (19.51%)፣ እንዲሁም ጉራጌ (16.34%)፣ ትግራዋይ (6.18%)፣ ስልጤ (2.94%)፣ እና ጋሞ (1.68%) ያጠቃልላል።

በአፍ መፍቻ ቋንቋነት የሚነገሩ ቋንቋዎች አማርኛ (70.99%)፣ አፋን ኦሮሞ (10.72%)፣ ጉራጌኛ (8.37%)፣ ትግርኛ (3.60%)፣ ስልጤ (1.82%) እና ጋሞ (1.03%) ይገኙበታል።

በ1999 በተካሄደው ሀገር አቀፍ የህዝብ ቆጠራ መሰረት 98.64 በመቶው የአዲስ አበባ መኖሪያ ቤቶች የንፁህ መጠጥ ውሃ ተጠቃሚ ሲሆኑ፣ 14.9% ንጹህ መጸዳጃ ቤት፣ 70.7% ጉድጓድ መጸዳጃ ቤቶች (አየር ማናፈሻም ያላቸውም ሆነ የሌላቸው) እና 14.3% የሚሆኑት የመጸዳጃ ቤት አገልግሎት አልነበራቸውም። የአዋቂዎች ማንበብና መጻፍ በሀገሪቱ በሁለቱም ፆታዎች ከፍተኛ ሲሆን ለወንዶች 93.6% እና ለሴቶች 79.95% ነው።

ከፌዴራል መንግሥት በተገኘው ኦፊሴላዊ አኃዛዊ መረጃ መሠረት በከተማው ውስጥ 119,197 የሚያህሉ ሰዎች በንግድና ንግድ ላይ ተሰማርተዋል; 113,977 በማኑፋክቸሪንግ እና በኢንዱስትሪ; 80,391 የተለያዩ የቤት ሰሪዎች; 71,186 በሲቪል አስተዳደር; 50,538 በትራንስፖርት እና በመገናኛ; 42,514 በትምህርት, በጤና እና በማህበራዊ አገልግሎቶች; 32,685 በሆቴል እና በመመገቢያ አገልግሎቶች; እና 16,602 በግብርና። ከተማዋ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በብዙ ቦታዎች ላይ በረጃጅም ሕንፃዎች ግንባታ ላይ ትገኛለች። የተለያዩ የቅንጦት አገልግሎቶችም እየታዩ ሲሆን የገበያ ማዕከላት ግንባታም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መጥቷል።

ዩኒቲ ፓርክ

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና መስሪያ ቤት በአዲስ አበባ ቦሌ አለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ቅጥር ግቢ ውስጥ ይገኛል።

ቱሪዝም በአዲስ አበባ እና በአጠቃላይ በኢትዮጵያ እያደገ ያለ ኢንዱስትሪ ነው። በ2007 የአውሮፓ የቱሪዝም እና ንግድ ምክር ቤት ኢትዮጵያን ለሀገር ውስጥ ቱሪዝም ምርጥ ሀገር ብሎ ሰይሟታል። የኮቪድ-19 ወረርሽኝ እና የትግራይ ጦርነት የቱሪዝም ቅነሳ አስከትሏል።

በ1987 በወጣው የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት የአዲስ አበባ ከተማ ተጠሪነታቸው ለኢትዮጵያ ፌዴራል መንግሥት ከሆኑ ሁለት የፌዴራል ከተሞች አንዷ ነች። ቀደም ሲል በ1983ቱ በኢትዮጵያ የሽግግር ቻርተር መሰረት የፌደራል አወቃቀሩን ተከትሎ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በወቅቱ ከነበሩት 14 ክልላዊ መንግስታት አንዱ ነበር። ነገር ግን ያ መዋቅር በፌዴራል ሕገ መንግሥት በ1987 ተቀይሮ አዲስ አበባ የክልልነት ደረጃ የላትም። የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አስፈጻሚ አካላቱን የሚመራ ከንቲባ እና የከተማውን ደንብ የሚያወጣ የከተማውን ምክር ቤት ያቀፈ ነው። ነገር ግን የፌዴራል መንግሥት አካል እንደመሆኑ መጠን የፌዴራል ሕግ አውጪው በአዲስ አበባ ውስጥ አስገዳጅ የሆኑ ሕጎችን ያወጣል። የከተማው ምክር ቤት አባላት በቀጥታ የሚመረጡት በከተማው ነዋሪዎች ሲሆን ምክር ቤቱ በተራው ደግሞ ከአባላቱ መካከል ከንቲባውን ይመርጣል። ለተመረጡት ባለስልጣናት የስራ ዘመን አምስት ዓመት ነው። ነገር ግን የፌደራሉ መንግስት አስፈላጊ ሆኖ ሲያገኘው የከተማውን ምክር ቤት እና አጠቃላይ አስተዳደሩን አፍርሶ ምርጫ እስኪደረግ ድረስ በጊዜያዊ አስተዳደር ሊተካ ይችላል። የአዲስ አበባ ነዋሪዎች በፌዴራል በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተወክለዋል። ነገር ግን ከተማዋ በፌዴሬሽን ምክር ቤት አልተወከለችም። በከንቲባው ስር ያለው አስፈፃሚ አካል የከተማውን ስራ አስኪያጅ እና የተለያዩ የሲቪል ሰርቪስ መሥሪያ ቤቶችን ያካትታል።

ከ2012 ጀምሮ ከታከለ ኡማ በኋላ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ የአዲስ አበባ ከንቲባ ሆነው በማገልገል ላይ ሲሆኑ፣ በከንቲባነት በመምራት የመጀመሪያዋ ሴት ናቸው።ከታከለ በፊት የፌዴራል መንግስት ከግንቦት 9 ቀን 1998 እስከ ጥቅምት 30 ቀን 2000 ያገለገሉትን ብርሃነ ደሬሳን በጊዜያዊ ባለአደራ ከንቲባነት እንዲመሩ ሾሟቸው ነበር። የዚህም ምክንያቱ በ1997 ዓ.ም ሀገር አቀፍ ምርጫ ገዥው ፓርቲ ኢህአዴግ በአዲስ አበባ ትልቅ ሽንፈት ቢያስተናግድም በአዲስ አበባ ያሸነፉት ተቃዋሚዎች በክልል እና በፌዴራል ደረጃ በመንግስት ውስጥ አልተሳተፉም። ይህ ሁኔታ አዲስ ምርጫ እስኪደረግ ድረስ በኢህአዴግ የሚመራው የፌደራል መንግስት ጊዜያዊ አስተዳደር እንዲመድብ አስገድዶታል።

ከቀዳሚዎቹ የአዲስ አበባ ከንቲቦች ፦ አርከበ ዕቁባይ (1995-1997)፣ ዘውዴ ተክሉ (1977-81)፣ ዓለሙ አበበ (1969-77) እና ዘውዴ ገብረሕይወት (1952-61) ይገኙበታል።

ታሪካዊ ምስሎች

[ለማስተካከል | ኮድ አርም]

የውጭ መያያዣ

[ለማስተካከል | ኮድ አርም]

የአዲስ አበባ ካርታ

  1. ^ "Census 2007 Tables: Addis Abeba" Archived 14 November 2010 at the Wayback Machine, Tables 2.1, 2.5, 3.1, 3.2 and 3.4. For Silt'e, the statistics of reported Shitagne speakers were used, on the assumption that this was a typographical error.
  2. ^ "DNA Studies Trace Migration from Ethiopia". bnd.com. St. Louis: Los Angeles Times. bnd. 22 February 2008. Archived from the original on 20 October 2007. Retrieved 20 July 2021.
  3. ^ Philip Briggs. Ethiopia. Bradt Travel Guides (2015) ገጽ. 49–50
  4. ^ Roman Adrian Cybriwsky, Capital Cities around the World: An Encyclopedia of Geography, History, and Culture, ABC-CLIO, USA, 2013, p. 6
  5. ^ Tufa, Dandena (2008). "Historical Development of Addis Ababa: plans and realities". Journal of Ethiopian Studies. 41 (1/2): 27–59. ISSN 0304-2243. JSTOR 41967609.
  6. ^ "City Profile Addis Ababa" Archived ፌብሩዌሪ 17, 2022 at the Wayback Machine (PDF). 17 February 2022.
  7. ^ አ.አ. ሚሌኒየም ጽ/ቤት አዲስ አበባ ባለፈውና በአዲሱ ሚሌኒየም ገጽ 20-23
  8. ^ "Archive copy". Archived from the original on 2012-12-14. በ2012-12-14 የተወሰደ.
  9. ^ "Archive copy". Archived from the original on 2013-10-16. በ2013-10-16 የተወሰደ.
  10. ^ "Archive copy". Archived from the original on 2013-01-11. በ2013-01-11 የተወሰደ.
  11. ^ "Archive copy". Archived from the original on 2013-11-25. በ2013-11-25 የተወሰደ.
  12. ^ "Archive copy". Archived from the original on 2013-11-05. በ2013-11-05 የተወሰደ.
  13. ^ "Archive copy". Archived from the original on 2013-12-03. በ2013-12-03 የተወሰደ.
  14. ^ "Archive copy". Archived from the original on 2013-12-03. በ2013-12-03 የተወሰደ.
  15. ^ "Archive copy". Archived from the original on 2013-12-03. በ2013-12-03 የተወሰደ.
  16. ^ "Archive copy". Archived from the original on 2013-01-04. በ2013-01-04 የተወሰደ.
  17. ^ "Archive copy". Archived from the original on 2013-01-25. በ2013-01-25 የተወሰደ.


ኢትዮጵያ

ታሪካዊ ቦታዎች አክሱምላሊበላጎንደርነጋሽሐረርደብረ-ዳሞአዲስ አበባ
አስተዳደራዊ ክልሎችትግራይአፋርአማራኦሮሚያሶማሌቤንሻንጉል ጉሙዝደቡብ ኢትዮጵያሲዳማማዕከላዊ ኢትዮጵያደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያጋምቤላሐረሪአዲስ አበባድሬዳዋ
ቋንቋዎችአማርኛግዕዝኦሮምኛትግርኛወላይትኛጉራጊኛሶማሊኛአፋርኛሲዳምኛሃዲያኛከምባትኛጋሞኛከፋኛሃመርኛስልጢኛሀደሪኛ
መልክዓ-ምድር - • አባይአዋሽራስ-ዳሽንሶፍ-ዑመርጣናደንከልላንጋኖአቢያታሻላ
ከተሞች - የኢትዮጵያ ከተሞች


%20its%20Prospects%20in%20the%20the%20new%20Millennium%28Amharic%29.pdf አ.አ. ሚሌኒየም ጽ/ቤት አዲስ አበባ ባለፈውና በአዲሱ ሚሌኒየም ገጽ 20-23]Delala addis ababa ethiopia